የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ ባለሞያዎች ማህበር ከማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ እና UN-WOMEN ጋር በመተባበር 29ኛውን ዓመታዊ ጉባኤ “Production and Use of Gender Statistics for Effective Implementation and Monitoring of Policy Commitments in Ethiopia” በሚል መሪ ቃል ከየካቲት 27-28/2013ዓ.ም በካፒታል ሆቴል አካሄደ፡፡
በዕለቱ የፕላን እና ልማት ኮሚሽን ሀላፊ ሚኒስትር ዶ/ር ፍጹም አሰፋ፣ የማዕካለዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ አመራሮች፣ የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ ማህበር አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተገኙ ሲሆን ጉባኤውን ሀላፊ ሚኒስትሯ በንግግር ከፍተውታል፡፡
በሀገራችን የሴቶች ተሳትፎና ውሳኔ ሰጪነት ከፍተኛ ቢሆንም የስርአተ-ፆታ መረጃ ማመንጨትና አቅርቦት ላይ ከፍተኛ ጉደለት እንዳለ የገለጹት ሀላፊ ሚኒስትሯ መረጃዎችን ወንድና ሴት ከማለት ባለፈ ሴቶች በማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ ና ኢኮኖሚያዊ ያላቸውን ተሳትፎና ወሳኝነት በግልጽ በመረጃ በማስደገፍ የማቅረብ ስራ መሰራት እንዳለበትና ሁሉም መረጃዎች ስርአተ-ፆታን በስታቲስቲክስ ውስጥ ማካተት እንዳለባቸው አያይዘው አስረድተዋል፡፡
ሀላፊ ሚኒስትሯ መንግስት ለፆታ እኩልነት ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱን፣ ስርአተ-ፆታን በስታቲስቲክስ ማካተትም ከ10ዓመቱ እቅድና ዘላቂ ልማት ግቦች ውስጥ አንዱ እንደሆነና በስታቲስቲክስ ስራ የተሰማሩ ባለሞያዎችና ተቋማትም ማንኛውንም መረጃ ስርአተ-ፆታን በግልጽ ባካተተ መልኩ መስራትና ለማህበረሰቡ ስለ ስርአተ-ፆታ ስታቲስቲክስ ጥቅም ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ መሰራት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲም በሚያጠናቸው ጥናቶች ስርአተ-ፆታን እንደሚያካትትና የሴቶችን ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎና ውሳኔ ሰጪነት የያዘ መረጃ ይፋ እያደረገ እንደሆነና በቀጣይም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል፡፡ በዕለቱ የማህበሩ አባላት ጥናታዊ ጽሁፎቻቸውን ካቀረቡ በኋላ ውይይት ተደርጎባቸው ጉባኤው ተጠናቋል፡፡