በአስተዳደራዊ መዛግብት መረጃ አያያዝና በኢትዮጵያ የመረጃ ጥራትና ግምገማ ማዕቀፍ ላይ የአቅም ግንባታ ስልጠና ከየካቲት 29/2013 ዓ.ም እስከ መጋቢት 4/2013 ዓ.ም ከደቡብና ከሲዳማ ክልል የመንግስት ተቋማት ተቋማት ለተውጣጡ 1000 ለሚሆኑ የግብርና፣ የጤና፣የወሳኝ ኩነትና የትምህርት ባለሙያዎች በአርባምንጭና በሀዋሳ የስልጠና ማዕከላት ስልጠና ተሰጠ።
በሀዋሳ የስልጠና ማዕከል የኤጀንሲው የብሔራዊ ስታቲስቲክስ ጥራትና ደረጃዎች ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዳምጠው ብርሃኑ በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለፁት ይህ ስልጠና በብሔራዊ ስታቲስቲክስ ስርዓት ውስጥ ያሉ ተቋማት በሀገር አቀፍ ደረጃ መደበኛ የሆነ የስታቲስቲክስ ስርዓት ለመፍጠር እንደሚጠቀም ገልፀዋል። አቶ ዳምጠው እንደገለፁት መደበኛ የሆነ ሰነድ በማዘጋጀትና በማሰራጨት ተቋማት የመረጃ ጥራትን ለማረጋገጥና ኤጀንሲው በብሔራዊ ስታቲስቲክስ ስርዓት ውስጥ ካሉ ተቋማት ጋር በመሆን ያለውን የመረጃ ክፍተት ለመሙላት ስልጠናው እንደሚጠቅም ገልፀዋል። የመረጃ ጥራት መገምገሚያ መስፈርቶች ስልጠና በመውሰድ በየተቋማችሁ ተግባራዊ ማድረግ አለባችሁ በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል።
የስልጠናው ዓላማ በብሔራዊ ስታቲስቲክስ ስርዓት ውስጥ ላሉ ተቋማት በአስተዳደራዊ መዛግብት መረጃ አያያዝና ጥራት ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር፣ ኤጀንሲውን ለማስተዋወቅ፣ የተለያዩ ተቋማት ባለሙያዎችን በስታቲስቲክስ ላይ ያላቸውን አቅምና ግንዛቤ ለማሳደግ እንደሆነ በስልጠናው መመሪያ ተገልጿል። ስልጠናው የስታቲስቲክስ መረጃዎች ያላቸውን ጠቀሜታ፣ የኤጀንሲውን ተግባር፣ ሀላፊነትና በኤጀንሲው ስለሚሰሩ ዋና ዋና ጥናቶች፣ የኢትዮጵያ የመረጃ ጥራትና ግምገማ ማዕቅፍ ፕሮግራምና ዲዛይን፣ የስታቲስቲክስ የመረጃ ምንጮችና የናሙና ጥናት ቆጠራ ያላቸውን ጠቀሜታ ላይ ትኩረቱን ያደረገ ስልጠና ተሰጥቷል። የስልጠናው ተሳታፊዎች በመረጃ ጥራት ላይና ስለኤጀንሲው ከዚህ በፊት ከነበራቸው የተሻለ ግንዛቤ ማግኘታቸውን ገልፀዋል።