ተቋሙ አምስተኛውን ዙር የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ጥናት ለማካሄድ ስልጠና በመስጠት ላይ ነው

የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ከአለም ባንክ /World Bank/ ጋር በመተባበር 5ተኛ ዙር የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ጥናት /Ethiopian Socioeconomic Survey/ ለማካሄድ ለ 468መረጃ ሰብሳቢዎች፣ 141ተቆጣጣሪዎችና 50ስታቲስቲሽያኖች በአዳማና ሐዋሳ ከተማ ከመጋቢት 05- 24/2014ዓ.ም ስልጠና በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡

ስልጠናውን በንግግር የከፈቱት የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢራቱ ይገዙ 5ተኛው ዙር የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ጥናት በገጠርና በከተማ የሚጠናና በየሁለት አመቱ በናሙና የተመረጡ ቤተሰቦችን በመከተል ያሳዩትን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች ለማወቅ የሚጠቅም መሆኑን ገልጸው ከጥናቱ የሚገኙ መረጃዎች  መረጃዎች ለፖሊሲ ቀረጻ፣ ለውሳኔ ሰጪዎች፣ በተለይ የግብርናውን ስታቲስቲክስ ለማዘመንና ለተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎች ቁልፍ ሚና ያለው በመሆኑ በመስክ መረጃ የመሰብሰብ ስራ ላይ የሚሰማሩ ባለሞያዎች በሙሉ መረጃውን በጥራት፣ በታማኝነትና ሀገራዊ ስሜት ጥናቱ ለታለመለት አላማ እንዲውል በትጋት እንዲሰሩ አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ጥናት አምስት ዙሮች ያሉት ሲሆን መረጃዎው ወካይ ከሆኑና በሳይንሳዊ መንገድ ከመላ ሀገሪቱ በተመረጡ 536የቆጠራ ቦታዎች ይሰበሰባል፡፡ በጥናቱ የመስክ ሥራ ላይ ለሚሳተፉት 468መረጃ ሰብሳቢዎች፣ 141ተቆጣጣሪዎችና 50ስታቲስቲሽያኖች በአዳማና ሐዋሳ ከተማ ለ20 ቀናት ስልጠና በመሰጠት ላይ ነው፡፡

ተቋሙ የመረጃ ጥራትንና ወቅታዊነትን ለማስጠበቅ ሙሉ በሙሉ የታብሌት ቴክኖሎጂን በመጠቀም ጥናቱን ያካሂዳል፡፡

የጥናቱን ውጤት በዋናነት መንግስት የሚጠቀምበት ሲሆን፤ ለኢንቬስተሮችና ለተመራማሪዎች ማህበረሰቡ በየጊዜው ያሳየውን የአኗኗር፣ የግብርናና የተለያዩ ለውጦችን  በማወቅ በቀጣይ ለሚደረጉ ምርምሮችና ጥናቶች እንደመነሻ ግብአትነት ያገለግላል፡፡