ሐምሌ 20/2015ዓ.ም አዳማ፤የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የ2015ዓ.ም የዕቅድ አፈፃፀም ግምገማና የ2016ዓ.ም ዕቅድ ዝግጅት ላይ ያተኮረ ውይይት ከሐምሌ 20-22/2015ዓ.ም በአዳማ ናፍሌት ሆቴል አካሄደ፡፡
የውይይት መድረኩን በንግግር የከፈቱት የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር በከር ሻሌ የውይይት መድረኩ ዋና ዓላማ በ2015ዓ.ም ዕቅድ ክንውን በመገምገም ከተሳኩት አፈፃፀም ለቀጣይ እንደጥሩ ልምድ በመውሰድ እንዲሁም ያልተሳኩት አፈፃፀሞች ለምን ማሳካት እንዳልተቻለ ችግሩን በመለየት በቀጣይ እንዳይደገሙ ለመስራት የሚያስችለን ግብዓቶችን ለማግኘት ታስቦ የተዘጋጀ መድረክ መሆኑን በመግለፅ ሁሉም ከተገኘው ውጤት እንዲሁም ካልተከናወኑ ተግባራት ድርሻው ምን እንደሆነ ወደውስጥ በማየት ፍሬያማ ውይይት እንዲደረግ አቅጣጫ በመስጠት የውይይት መድረኩን አስጀምረዋል፡፡ በውይይት መድረኩ የ2015ዓ.ም የዕቅድ አፈፃፀምና ለ2016ዓ.ም የተዘጋጀው ዕቅድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
በውይይቱ ማጠቃለያ ከተደረሰበት ግምገማ የተቋሙ የ2015ዓ.ም ዕቅድ አፈፃፀም 85.5 በመቶ መሆኑ በበጀት ዓመቱ ተቋሙ ከፍተኛ የሚባል የበጀት ችግር ውስጥ የነበረበትና በሌላ መልኩ መጠነ ሰፊ ተቋማዊ ሪፎርም የተካሄደበት ዓመት ነበር፡፡ በዚህም ተቋሙ በቀጣይ ብዙ ዓመታት ወደፊት መውሰድ የሚያስችል መዋቅር የማዘጋጀት ተግባር ተጠናቆ በቅርብ ጊዜ ተፈቅዶ ተግባራዊ እንደሚደረግ በሌላ መልኩ መረጃ ከማመንጨት አንፃር ቀላል በሚባሉ የሀገሪቷ አካባቢዎች የፀጥታ ችግር እያለም ቢሆን በመስክ ስራው የሚሳተፉ ሰራተኞች ጥንካሬና አመራሩ በሰጠው ድጋፍ ወርሀዊ የዋጋ ግሽበት፣ የግብርና ዘርፍ ናሙና ጥናት፣ የቆጠራ ካርታን ወቅታዊ የማድረግ ተግባራት በስኬት የሚጠቀሱ ሲሆኑ የበጀት አስተዳደርና የግዢ ተግባራት እንዳለፈው ዓመት ሁሉ በዚህ ዓመት ያልታሻገርናቸው ችግሮቻችን ሆነው የቀጠሉ መሆኑን የገለፁት ዋና ዳይሬክተሩ በ2016ዓ.ም እነዚህን ችግሮች በተለየ ትኩረት ለመፍታት የሚሰሩ እንደሆነና ችግሮቻችን ላለመፈታት ምክንያት የሆኑ አካላት ላይም አስፈላጊው እርምጃ እንደሚወሰድ አስረድተዋል፡፡
ለ2016ዓ.ም የተዘጋጀው የፕሮግራም በጀት ዕቅድ ቀርቦ ውይይት የተደረገበት ሲሆን ለበጀት ዓመቱም መንግስት 476,553,450 ብር የመደበ ሲሆን ከሌላ ጊዜ ጋር ሲነፃፀር የተመደበው በጀት ቅናሽ ያለው በመሆኑ በተመደበው በጀት ቅድሚያ ሰጥተን መስራት በምንችለው ላይ ትኩረት በማድረግ መስራት እንደሚገባ በሌላ መልኩ ከመንግስት ውጪ ያሉት ለጋሾች የሚሰጡንን ገንዘብ በአግባቡና ለተገቢ ተግባር በመጠቀም የበጀት ቅናሹን ለማሟላት ጥረት እንደሚደረግ ታውቆ ከ2015ዓ.ም የተገኙትን ጥሩ ልምዶችን በማጠናከር እንደችግር የተለዩትን ለመፍታት በጋራ እንደቡድን ሰርተን ውጤታማ የምንሆንበት ዓመት እንዲሆን መትጋት እንዳለብን አቅጣጫ በመስጠት ውይይቱ ተጠናቋል፡፡ በውይይቱ የዋናው መስሪያ ቤት ሁሉም የስራ ክፍል ሀላፊዎችና የ25ቱ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ስራ አስፈፃሚዎች ተሳትፈዋል፡፡