የፕላንና ልማት ኮሚሽንና ተጠሪ ተቋማት “ኑ ኢትዮጵያን እናልብሳት” መርሀግብር አካሄዱ

“ኑ ኢትዮጵያን እናልብሳት” በሚል መሪ ቃል የፕላን እና ልማት ኮሚሽን፣ የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ እና የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት በጋራ በመሆን በ22/11/2013ዓ.ም በአማራ ክልላዊ መንግስት ሰሜን ሸዋ ዞን በሸዋ ሮቢት ከተማ የሮቢ ዙጢ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት የክረምት ችግኝ ተከላ እና የበጎ አድራጎት መርሀ ግብር አከናወኑ፡፡

በመራሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት በሚኒስቴር ማዕረግ የፕላንና ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር ፍጽም አሰፋ ካለፉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት በየአመቱ በክረምት በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን የተጀመረው የአረንጋዴ አሻራ ዘመቻ አካል በመሆን የሦስቱ ተቋማት አመራርና ሠራተኞች ችግኝ በመትከል የበኩላቸውን ሲወጡ መቆየታቸው ተጠቅሶ በዚህ አመት ሁሉም የፌደራል መንግስት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችና ኤጀንሲዎች “ኑ ኢትዮጵያን እናልብሳት” በሚል መሪ ቃል ከዋና ከተማ ዙሪያ ወጣ ባለ መልኩ ከታችኛው ህብረተሰብ ጋር በመገናኘት የችግኝ ተከላና የበጎ አድራጎት ተግባራት እንዲያከናውኑ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የፕላንና ልማት ኮሚሽንና ተጠሪ ተቋማት አመራሮችና ሰራተኞች በአማራ ክልላዊ መንግስት ሰሜን ሸዋ ዞን በሸዋሮቢት ከተማ አስተዳደር ህብረተሰባችን መሀል ተገኝተን ይህን ተግባር ስንፈጽም ከፍተኛ ክብር እንደሚሰማቸው በመግለጽ መርሀ ግብሩን አስጀምረዋል፡፡  


በመርሐ ግብሩ በሸዋ ሮቢት ከተማ የሚገኘው የሮቢ ዙጢ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ውስጥ በተዘጋጀው 1500 የችግኝ ጉርጓዶች የጽድና ፓፓያ ችግኝ ተከላ እንዲሁም የዙጢ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት አምስት የመማሪያ ክፍሎች ሙሉ ዕዳሳት ማስጀመር ፕሮግራም ተካሂዷል፡፡

በተጨማሪም በከተማ አስተዳደሩ ለሚገኙት ት/ቤቶችና ተቋማት የሚውሉ 7ኮምፒውተሮች፣ 7 ፕሪንተሮች፣ 7 ፎቶ ኮፒ ማሽኖች፣ 7ውሃ ማጣሪያና እና 100 የአጥር ቆርቆሮ ስጦታ ለከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ወ/ሮ ሉባባ መኮንን አስረክበዋል፡፡

በዚህ ፕሮግራም ከሦስቱ ተቋማት የተወጣጡ 120 ሰዎች የተሳተፉ ሲሆን በቀጣይ ለተተከሉት ችግኞች ክትትል እንዲሁም የትምህርት ቤቱ የመማሪያ ክፍሎች ዕድሳት በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቀው አስፈላጊው ርክክብ እንደሚደረግ ለማወቅ ተችከሏል፡፡