ለአራተኛ ጊዜ ሲካሄድ የነበረው የሀገር አቀፍ የሰው ሀይልና ፍልሰት ጥናት ለመረጃ ተጠቃሚዎች ይፋ ተደረገ

የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ የ2013 ዓ.ም ሀገር አቀፍ የሰው ሀይልና ፍልሰት ጥናት ሪፖርት ለመረጃ ተጠቃሚዎች ነሀሴ 11/2013 ዓ.ም በስካይላይት ሆቴል ይፋ አደረገ፡፡

የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢራቱ ይገዙ ሲሆኑ በንግግራቸው እንደገለፁት ለመጀመሪያ ጊዜ የሰው ሀይል ጥናት ከፍልሰት ጥናት ጋር ተቀናጅቶ የተሰራ ጥናት መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ጥናቱን ለማካሄድ ተቋሙ ሰፊ ዝግጅት በማድረግና ለመረጃ ሰብሳቢዎች፣ ስታቲሽያኖችና ሱፐርቫይዘሮች ስልጠና በመስጠት ጥራቱን የጠበቀ መረጃ ለመረጃ ተጠቃሚው እንዲደረስ ከፍተኛ ስራ መሰራቱን አስታውሰዋል፡፡

የጥናቱ ዋና ዓላማ ለፖሊሲ አውጪዎች፣ ለተመራማሪዎች እና ለተለያዩ ተቋማት ውሳኔ ለመስጠት የሚያስችል ጥናት እንደሆነ ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡

በጥናቱ መሰረት በሀገር አቀፍ ደረጃ የተሳትፎ ምጣኔ 65 በመቶ ሲሆን ይህም ማለት ከ100 ለስራ ከደረሱ ሰዎች 65 በመቶ የሚሆኑ ዜጎች በምርት ስራ ለመስራት ዝግጁ እንደሆነ ከጥናቱ ሪፖርት መረዳት ይቻላል፡፡

የስራ አጥነት ምጣኔው በሀገር አቀፍ ደረጃ 8 በመቶ (3,608,688) ዜጎች ስራአጥ ሲሆኑ ከጾታ አንጻር በሴቶች 11.7 በመቶ በማስመዝገብ ከፍተኛውን ቁጥር ሲይዙ በአንፃሩ በወንዶች 5 በመቶ ሲሆን በከተማ 17.9 በመቶ በማስመዝገብ ከፍተኛው የስራአጥ ቁጥር ሲኖር በአንፃሩ በገጠር 5.2 በመቶ መመዝገቡን የጥናቱ ሪፖርት ያመላክታል፡፡

የስራጥነት ሁኔታው ከክልሎች እና ከተማ መስተዳድሮች አንጻር ሲታይ ከፍተኛው ስራአጥ ቁጥር በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር 22 ከመቶ በተከታይነት ድሬደዋ 16 ከመቶ ሲያስመዘግቡ ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል 4.3 ከመቶ  ዝቅተኛውን የስራአት ቁጥር ተመዝግቧል፡፡

የፍልሰት ምጣኔ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከአጠቃላይ ህዝብ ቁጥር ውስጥ 17.1 በመቶ የፈለሱ ሲሆኑ ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገው ፍልሰት 32 በመቶ በመሆን ከፍተኛውን ቁጥር ይዟል፡፡

በክልሎች የሚደረግ የፍልሰት ምጣኔ 292 የሚሆኑ ዜጎች ወደ አዲስ አበባ ሲፈልሱ በሌላ በኩል አማራ ከ1000 ሰዎች 56 የሚሆኑ ዜጎች፤ በደ/ቡ/ብ/ሕ ከ1000 ሰዎች 33 የሚሆኑ ዜጎች ወደ ሌላ ክልል የሚፈልሱ መሆናቸውን ጥናቱ ይገልፃል፡፡

አለም አቀፍ ፍልሰት ከስደት ተመላሽ 77 በመቶ ከመካከለኛው ምስራቅ የተመለሱ፤ 13 በመቶ የሚሆኑት ከአፍሪካ ሀገሮች የተመለሱ ሲሆኑ፣839,224 ከሀገር ውጪ የሚኖሩ ዜጎች  ናቸው፤ አድራሻቸው የማይታወቅ ዜጎች ወደ ውጪ ሀገር ሂደው ነገር ግን ያሉት ሁኔታ የማይታወቅ 51,089 ሊደርሱ እንደሚችሉ መረጃው ያመላክታል፡፡

ሌላው በጥናቱ የተካተተው ስለኮረና ቫይረስ ቤተሰቦች ያላቸው ግንዛቤ፣ መከላከልና ያደረሰው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተፅዕኖ ሲሆን ከአጠቃላይ ቤተሰቦች ውስጥ 84,75,53,40 እጅ መታጠብ፣ ማስክ ማድረግ፣ ርቀት መጠበቅ፣ አልኮል/ ሳይኒታይዘር መጠቀም ኮረናን ለመከላከል ግንዛቤ በቅደም ተከተል መረጃው የሚያሳይ ሲሆን ከአጠቃላይ ቤተሰቦች ውስጥ 72,57,33ና 28 በመቶ እጅን መታጠብ፣ ማስክ ማድረግ፣ ርቀትን መጠበቅ፣ አልኮል/ ሳኒታይዘር በመጠቀም ኮረናን እንደሚከላከሉ በቅደም ተከትል ገልፀዋል፤ 44 በመቶ የሚሆኑት ቤተሰቦች በኮረና ምክንያት ገቢያቸው እንደቀነሰ የጥናቱ ሪፖርት ያመላክታል፡፡

ጥናቱ ከጥር እስከ የካቲት 2013 ዓ.ም መረጃው ከመስክ የተሰበሰበ ሲሆን ጥናቱን ለማካሄድ ከመንግስትና ከአለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት (IOM) በተደረገ ድጋፍ ጥናቱ ሊካሄድ መቻሉን ተገልጿል፡፡

ጥናቱ ከትግራይ ክልል በስተቀር በሁሉም ክልሎች በናሙና ከተመረጡ 49,919 ቤተሰቦች የጥናቱ መረጃዎች ተሰብስበዋል፡፡