በሀገርአቀፍ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ የስርዓተ ፆታ የንብረት ባለቤትነት ጥናት ለማካሄድ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል

በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የስርዓተ-ፆታ የንብረት ባለቤትነት (Gender Asset Gap Survey) ለማካሄድ ከየካቲት 8 እስከ 15/2013 ዓ.ም በአዳማ ከተማ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል፡፡

በስልጠናው መክፈቻ ላይ የኤጀንሲው የስታቲስቲክስ ጥናቶችና ቆጠራዎች ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ አማረ ለገሰ እንደገለፁት ስርዓተ-ፆታን መሰረት ያደረገ የንብረት ባለቤትነት አያያዝ ስታቲስቲካዊ መረጃዎች የሴቶችን አቅም ማጎልበት፣ ደህንነትና ተጋላጭነትን ለመቀነስና አኗኗር በተመለከተ ለሚዘጋጁት ዕቅዶችና ፖሊሲዎች በግብዓትነት እንደሚያገለግሉ ገልፀዋል፡፡

በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የሚጠና ጥናት ሲሆን ሴቶችን ከማብቃትና የስርዓተ-ፆታ እኩልነት ከማምጣት አኳያ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው የቤተሰብ ጥናቶችና ዋጋዎች ስታቲስቲክስ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አለማየሁ ተፈሪ በማከል ገልፀዋል።

የስርዓተ-ፆታ የንብረት ባለቤትነት ጥናት በሀገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚጠና ጥናት ሲሆን በቤተሰብና በግለሰብ ደረጃ ያሉ የንብረት ባለቤትነትና አያያዝ ላይ መረጃዎችን ያስገኛል፡፡ የጥናቱ ዋና ዓላማ በሴቶችና በወንዶች መካከል ያለውን የንብረትና የባለቤትነት አያያዝ ልዩነት ለማወቅ የሚያስችልና የስርዓተ-ፆታን እኩልነትን ለማምጣት የተገቡ ሀገራዊና አለም አቀፋዊ ስምምነቶችን አፈፃፀም ለመከታተልና ለመገምገም የሚያስችል መረጃዎችን ማመንጨት ነው፡፡ በዚህም በሴቶችና በወንዶች መካከል የንብረት ባለቤትነት ልዩነት መገንዘብ፣ የስርዓተ-ፆታ ሀብት ልዩነት መለካት፣ ቤተሰብ ውስጥ የስርዓተ-ፆታ የንብረት ባለቤትነትና ሀብት ተለዋዋጭነት መገንዘብ እንደሆኑ በስልጠናው መመሪያ ላይ ተገልጿል፡፡

መረጃው በገጠርና በከተማ 442 የቆጠራ ቦታዎች የሚሸፍንና በናሙና ከተመረጡ 24‚200 ቤተሰቦች የሚሰበሰብ ሲሆን በገጠርና በከተማ ከእያንዳንዱ የቆጠራ ቦታ 22 ቤተሰቦች በመምረጥ መረጃው በታብሌት ቴክኖሎጂ የሚሰበሰብ ይሆናል። በአሰልጣኞች ስልጠና ከዋናው መ/ቤትና ከቅ/ጽ/ቤት ለተውጣጡ 60 ባለሙያዎች የተሰጠ ሲሆን ከየካቲት 18 እስከ 25/2013 ዓ.ም ለመረጃ ሰብሳቢዎች በሶስት ማዕከላት የሚሰጥ ይሆናል፡፡ ከመጋቢት 1/2013 ዓ.ም እስከ ሚያዚያ 15/2013 ዓ.ም መረጃው ከመስክ የሚሰበሰብ ሲሆን በስራው ላይ 658 ወንድና 658 ሴት መረጃ ሰብሳቢዎች በአጠቃላይ 1316 የሚሆኑ መረጃ ሰብሳቢዎች በጥናቱ እንደሚሳተፉ ከወጣው መርሀ ግብር ለመረዳት ተችሏል፡፡