በብሔራዊ ስታቲስቲክስ ልማት ስትራቴጂክ ዕቅድ ላይ ውይይት ተካሄደ

የማዕከላዊ ስታቲሰቲክስ ኤጀንሲ በሦስተኛው አምስት አመት ብሄራዊ ስታቲሰቲክስ ልማት ስትራቴጂክ ዕቅድ እንዲሁም አስር ዓመት ስታቲሰቲክስ ልማት ሮድ ማፕ (Rod Map) ላይ ከነሐሴ 24-26/2013ዓ.ም በቢሾፍቱ ፒራሚድ ሪዞርትና ሆቴል ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሄደ፡፡

የውይይት መድረኩን በንግግር የከፈቱት የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወ/ት አበራሽ ታሪኩ ኤጀንሲው በሚቀጥሉት አስር አመታት ሊሰራ ያሰባቸውን የስታቲስቲክስ ሲስተሙን ማስተባበርና ማቀናጀት፣ የብሄራዊ ስታቲስቲክስ መረጃን ማዘመንና ማስተዳደር፣ አቅም ማጎልበት፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር ስትራቱጂክ አጋርነት መፍጠር፣ የስታቲስቲክስ መረጃዎች ላይ የተለያዩ ስልጠናዎችን መስጠትና የመረጃ አጠቃቀም ላይ ሰፊ ስራ መስራት ዋና ዋና የረጅም ጊዜ ዕቅዶች እንደሆኑ ጠቅሰው በሶስተኛው የአምስት አመት የስታቲስቲክስ የስራ ዕቅድ  (NSDSIII) የስታቲስቲክስ ህጉን ማሻሻል፣ የብሄራዊ ስታቲስቲክስ ስርዓቱን ማስተባበርና ማጠናቀር፣ የመረጃ ጥራትን ማስጠበቅ፣ የመረጃ ስርጭትና ተደራሽነት እና የአይሲቲ አጠቃቀምን ማዘመን ላይ ማተኮሩን መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ም/ዋ/ዳሯ አያይዘውም ዕቅዱ የተዘጋጀው ከሴክተር መ/ቤቶችና ከባለድርሻ አካላት ያሉትን የመረጃ ፍላጎቶች፣ ያለፈውን የአምስት አመት የስራ ዕቅድ አፈጻጸም፣ የቀጣይ አስር አመት ዕቅድ መመዘኛ ስርዓትና ዘላቂ የልማት ግቦችን እንደ ዋና ግብአትነት በመጠቀም እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ መድረኩ የተዘጋጀው በዕቅዱ ከሴክተር መ/ቤቶችና ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጎበት ለማዳበር እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

በዕለቱ የቀጣይ አስርና አምስት ዓመት ዕቅድ ላይ ሰፊ ማብራሪያ ቀርቦ ከተሳታፊዎች ውይይትና አስተያየት ተሰትቶበታል፡፡

በውይይት መድረኩ የማዕካላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ከፍተኛ አመራሮች፣ ከፍተኛ ባለሞያዎችና ከ23 በላይ ሴክተር መ/ቤቶች የተሳተፉ ሲሆን የአለም ባንክ፣ የተባበሩት መንግስታት ስታቲስቲክስ ክፍልና የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ለውይይት መድረኩ የቴክኒክና የገንዘብ ድጋፍ አድረገዋል፡፡