በተዘጋጀው የሜታዳታ መጽሀፍ ላይ ውይይት ተደረገ

ሜታዳታ መጽሀፍ (Metadata handbook) ላይ ከጥቅምት 30 እስከ ህዳር 4/2014 ዓ.ም ከማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲና ከተለያዩ ተቋማት ከተውጣጡ ባለሙያዎች ጋር ውይይት ተደረገ።

መድረኩን በንግግር የከፈቱት የኤጀንሲው ም/ዋና ዳይሬክተር ወ/ሪት አበራሽ ታሪኩ ሜታዳታ መጽሀፉ በሀገራችን በዘላቂ ልማት ግቦች ላይ የሚገኙ አመላካቾችን መሰረት አድርጎ የተዘጋጀ ሲሆን አመላካቾች መደበኛ የሆነ ትርጓሜና ማብራሪያ እንዲኖራቸው እንዲሁም የመጽሀፉ ተጠቃሚዎች የጠራ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ስለሚረዳ መጽሀፉ ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑን ገልፀዋል።

ይህ ሜታዳታ መጽሀፍ (Metadata handbook) በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀ ሲሆን 17 ግቦች፣ 169 የሚሆኑ አመላካቾችን የያዘ ሲሆን በቀጣይ 15 ዓመታት ለሚተገበረው ለዘላቂ ልማት ግብ አጀንዳ እንደማዕቀፍ ያገለግላል።

በተጨማሪም ሜታዳታ መዝገበቃላት (Metadata dictionary) ያስፈለገበት ምክንያት በብሔራዊ ስታቲስቲክስ ስርዓት ውስጥና ሌሎች መረጃ አመንጪዎችና መረጃ ተጠቃሚዎች መካከል መደበኛ የሆነ የአመላካቾች ትርጓሜ እንዲኖር ለማድረግ ነው ተብሏል። ጥራቱን ጠብቆ የተዘጋጀ ሜታዳታ መጽሀፍ ለአንድ ተቋም ግልጽ የሆነና ጥራት ያለው መረጃ እንዲያቀርብ ያደርገዋል ሲሉ መጽሀፉን ያዘጋጁት አማካሪ ገልጸዋል።

ሜታዳታ ማዘጋጃ የራሱ የሆነ ቴምፕሌት ያለው ሲሆን በኤሌክትሮኒክስ ማዘጋጃ ዘዴ SDMX የተሞከረ ሲሆን በዚህ ቴምሌት መሰረት እያንዳንዱ አመላካች የያዘና ስለአመላካቹ አጠቃላይ መረጃ፣ መረጃውን ሪፖርት የሚያደርገው ፣ የአመላካቹን ትርጓሜ፣ ጽንሰ ሀሳቦችና ምድቦቹን፣ የመረጃውን ምንጭና መረጃው የተሰበሰበበትን ዘዴ፣ ሌሎች የሜቶዶሎጂ ግብዓቶች፣ የመረጃው መገኘትና ማካተት ሁኔታ፣ አለም አቀፍ የመደበኛ /ንፅፅር በሜታዳታ ቴምፕሌት ላይ የሚካተቱ መሆናቸው ተገልጿል።

በመድረኩ ሜታዳታ ቴምፕሌቱን ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ ባለሙያዎች የተቋማቸው መረጃ ወደቴምፕሌቱ በማስገባት የሞከሩት ሲሆን ማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ እንደግብዓት በመውሰድ የመጨረሻውን ሜታዳታ መጽሀፍ ለማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ እንደሚሰጥ ተገልጿል።

ሜታ ዳታው ሲዘጋጅ የተለያዩ ተግዳሮቶች ያጋጠሙ ሲሆን በዋነኛነት በተለያዩ ተቋማት ያሉ ባለሙያዎች ስለሜታዳታና ስለዘላቂ ልማት ግቦች ግንዛቤና እውቀት ማነስ፣የሜቶዶሎጂ ሰነዶችን በቀላሉ መጠቀም አለመቻል፣ የሚመለከታቸው ተቋማትና ባለድርሻ አካላት ምላሽ መዘግየትና ሌሎችም ችግሮች ነበሩ።

በሜታዳታ ዙሪያ ለማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲና ለሚመለከታቸው አካላት ስልጠና መስጠት፣ መጽሀፉን በቀላሉ መጠቀም እንዲቻል ማሳተምና ድረ-ገጽ ላይ መጫን፣ሜታዳታ መጽሀፉን ተገቢነቱን ለመጠበቅ ማሻሻልና ለባለድርሻ አካላት ግንዛቤ መፍጠር እንደመፍትሔ ተቀምጠዋል።

በመድረኩ ከማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲና ከብሔራዊ ስታቲስቲክስ ስርዓት ተቋማት የተውጣጡ 45 ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።