የፕላንና ልማት ኮሚሽንና የተጠሪ ተቋማት ሰራተኞች ለሀገራቸው ዘብ እንደሚቆሙ ገለፁ፡፡

መከላከያን በመደገፍ ለሀገራችን ህልውናና ሉዓላዊነት ሁላችንም ዘብ እንቆማለን በሚል መሪ ቃል የፕላንና ልማት ኮሚሽን፣የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ እና የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ሰራተኞችና አመራሮች በ 03/12/2013 ዓ.ም በማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ የስብሰባ አዳርሽ ውይይት አደረጉ፡፡

የኢፌዴሪ ፕላንና ልማት ኮሚሽን ተጠሪ ተቋማት ከሆኑት የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ እና የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት አመራሮች እና ሠራተኞች ባደረጉት ውይይት የአንድ ወር ደመወዛቸውን ለመስጠት ቃል ገብተዋል፡፡ 

በተጨማሪም የደም ልገሳና የተለያዩ ቁሳቁሶችን ድጋፍ ለማድረግ የሶስቱም ተቋማት ሰራተኞች ቃል የገቡ ሲሆን በተከታታይ ድጋፍ ለማድረግ ለመከላከያ ሰራዊት ደጀን መሆናቸውን ለማሳየት ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልፀዋል፡፡

እኛ የምንኖረው ሀገር ስትኖር ነው ያሉት አመራርና ሰራተኞቹ፤ ሀገር አፈርሳለሁ ብሎ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘውን ሀይል መመከት የሁሉም ሃላፊነት መሆኑን ያመለከቱ ሲሆን አስፈላጊ ከሆነ ግንባር ድረስ እንደሚሄዱም ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል፡፡ 

የፕላንና ልማት ኮሚሽነሯ ዶ/ር ፍፁም አስፋው እንደገለፁት ሰራተኛው ያሳየው ተነሳሽነት ያደነቁ ሲሆን ከደሞዝ ድጋፍ አልፎ ለአገር ሉዓላዊነት መከበር ግንባር ድረስ ለመዝመት ባሳዩት ቁርጠኛነት ኩራት እንደተሰማቸው ገልፀዋል፡፡

ሰራተኞቹ በየተመደቡበት የስራ መስክ ስኬት ለማምጣት ከመቸውም ጊዜ በላይ ጊዜ ሰጥተው እየሰሩ መሆኑን ዶክተር ፍፁም አስፋው የተናገሩ ሲሆን ሁሉም በተሰማራበት ስራ ግዜ በመስጠት ውጤታማ በመሆን ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡