የ2014ዓ.ም ሰፋፊና መካከለኛ የንግድ እርሻዎች ጥናትን ለማካሄድ ዝግጅቱ ተጠናቋል

የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የ2014ዓ.ም የሰፋፊና መካከለኛ የንግድ እርሻዎች ጥናትን ለማካሄድ ከህዳር 13-25/2014ዓ.ም በአዳማ ኮንፈርት ሆቴል ስልጠና ሰጠ፡፡

በስልጠናው የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት የግብርና ተፈጥሮሃብትና ከባቢ ስታቲስቲክስ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አህመድ እብራሂም ካለፉት አመታት ተሞክሮዎች በመነሳት በዘንድሮው የሰፋፊና መካከለኛ የንግድ እርሻዎች ጥናት ብዙ የመጠይቅ ማሻሻያዎች እንደተደረጉ ገልጸው፤ የሃገሪቱ አስር አመት የልማት ዕቅድ ላይ መመለስ አለባቸው የተባሉ ዋና ዋና አመላኮቾችን በጥናቱ እንዲመሉ ማሻሻያዎቹ እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡ ስታቲስቲሺያኖች፣ ተቆጣጣሪዎችና መረጃ ሰብሳቢዎች መረጃዎቹን በጥራትና በወቅቱ ለመሰብሰብ የቅንጅት ስራ መስራት እንዳለባቸው የስራ አቅጣጫ ሰተዋል፡፡

የሰፋፊና መካከለኛ የንግድ እርሻዎች ጥናት ሀምሳና ከዚያ በላይ ሄክታር የመሬት ስፋት መጠንና የቤት እንስሳት ብዛት ያላቸውን ባለሀብቶች ወይም ኢንቬስተሮች በቀጥታ ወደ ጥናቱ በማስገባት እንዲሁም ከሀምሳ በታችና እስከ አስር ሄክታር የመሬት ስፋት መጠንና የቤት እንስሳት ብዛት ያላቸውን ባለሀብቶች ወይም ኢንቬስተሮች በናሙና በመምረጥ የመሬት ስፋት፣ ምርትና ምርታማነትን፣ የሰብል አይነትን (በሀገር አቀፍ፣ በክልልና በዞን)፣ የእርሻውን አጠቃላይ ሁኔታ፣ ጥቅም ላይ የዋለ ማዳበሪያን፣ ምርጥ ዘር፣ የአካባቢ ዘር፣ የፀረ-ሰብል መድኃኒትን እንዲሁም ፣የቤት እንስሳት (በብዛት፣ በአይነት፣ በዕድሜ፣ በፆታና በአገልግሎት)፣ የተመለከቱ ዝርዝር መረጃዎች የሚሰበሰቡበት ሀገር አቀፍ ሽፋን ያለው ጥናት ነው፡፡

ለጥናቱ በ20ቅ/ጽ/ቤቶች ከ2510የእርሻ አልሚዎች በመጠይቅ መረጃ ይሰበሰባል፡፡ በጥናቱ 21 ስታቲስቲሽያኖች፣33 ተቆጣጣሪዎችና 102 መረጃ ሰብሳቢዎች ይሳተፉበታል፡፡ በመስክ ላይ የመረጃ አሰባሰብ ሙሉ በሙሉ የታብሌት ቴክኖሎጂን በመጠቀም የሚከናወን ሲሆን ይህም የመረጃ ጥራትና ወቅታዊነትን ከመጨመርና ለጥናቱ የሚወጣውን ወጪ ከመቀነስ አናጻር የጎላ ሚና አለው፡፡

ለጥናቱ በመስክ ከህዳር30 እስከ ጥር 30/2014ዓ.ም መረጃዎች የሚሰበሰቡ ሲሆን ሚያዝያ 1/2014ዓ.ም ለተጠቃሚዎች ይፋ እንደሚደረግ ይጠበቃል፡፡ የጥናቱን ውጤት በዋናነት መንግስት ለሚያካሂዳቸው አዳዲስ ፖሊሲዎችና የረዥምና ለአጭር ጊዜ ዕቅዶችና በዘርፉ ያለውን የታረሰ የመሬት ስፋት፣ ምርትና ምርታማነት ለማወቅ የሚጠቀምበት ሲሆን፣ በዘርፉ ለተሰማሩ ኢንቬስተሮችና ተመራማሪዎች ለምርምርና ጥናቶቻቸው እንደመነሻ ግብዓትነት ያገለግላል፡፡