
የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ የ2013 ዓ.ም የቤተሰብ ተኮር የኑሮ ሁኔታ ስታቲስቲክስ ጥናት ለማካሄድ ከህዳር14-25/2013 ዓ.ም በአዳማ ድሪምቪው ሆቴል ከሁሉም ቅ/ፅ/ቤቶችና ከዋናው መ/ቤት ለተውጣጡ 53 ስታቲሽያኖች ስልጠና ተሰጠ፡፡
የቤተሰብ ተኮር የኑሮ ሁኔታ ክትትል ስታቲስቲክስ ጥናት በዋነኝነት በድህነትና በደህንነት ሁኔታዎች ላይ በማተኮርና አጠቃላይ የህዝቡን የኑሮ ሁኔታና ደረጃ በማሳየት ከፍተኛ አስተዋፆ የሚያበረክት ጥናት ነው፡፡ በመሆኑም የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ከ1988 ዓ.ም ጀምሮ መደበኛ መርሀግብር በመንደፍ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ደህንነት ጥናት መረጃዎችን በመሰብሰብ፣በማጠናቀርና በመተንተን ለመረጃ ተጠቃሚዎች ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ ጥናቱ በየአምስት ዓመቱ በሀገርአቀፍ ደረጃ ሲካሄድ የቆየ ሲሆን ዘድሮም ለስድስተኛ ጊዜ ይካሄዳል፡፡
ጥናቱ ከዚህ በፊት የቤተሰብ ፍጆታና ወጪ ጥናትና የኢኮኖሚና ማህበራዊ ደህንነት ጥናት በተናጠል በተለያየ መረጃ ሰብሳቢና መጠየቅ መረጃው ሲሰበሰብ የቆየ ቢሆንም በታየው የመረጃ ጥራት ክፍተት ዘንድሮ ሁለቱን ጥናቶች በማጣመር የቤተሰብ ተኮር የኑሮ ሁኔታ ክትትል ስታቲስቲክስ ተብሎ በጥምረት በአንድ መጠይቅና መረጃ ሰብሳቢ በጥምረት እንዲጠኑ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል።
የጥናቱ አላማዎች የማሀበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕቅዶችን እንዲሁም የፖሊሲ ውሳኒዎችን ለማመንጨት የሚረዳ መረጃ ማስገኘት፣ በየደረጃው የሚገኘው (አገርአቀፍና ክልል) የገጠርና የከተማ ህብረተሰብ የሚመገበውን፣የሚጠጣውን የምግብናየመጠጥ ፍጆታ እንዲሁም የሌሎች ዕቃዎችና አገልግሎቶች መጠን አይነትና ዋጋ ለመገምገም፣የተለያዩ መጠን ያላቸው ቤተሰቦች የፍጆታ መጠንና ልዩነት ግብአት ለማወቅና በርካታ አላማዎች ያሉት ጥናት ነው፡፡

ጥናቱ የሚካሄደው ከጥር1/2013-ታህሳስ30/2014ዓ.ም ድረስ በገጠርና በከተማ በሳይንሳዊ መንገድ በተመረጡ በአጠቃላይ 2,088 የቆጠራ ቦታዎችና 37,584 ያህል ቤተሰቦችን በመሸፈን የወቅቱ በሽታ ኮቪድ-19ን በመከላከል አመቱን በሙሉ ጥናቱ ይካሄዳል፡፡ በአጠቃላይ የቤተሰብ ተኮር ሁኔታ ስታቲስቲክስ ጥናት በዘመናዊ የታብሌት ቴክኖሎጂ የሚታገዝ የሰው ሀይል በዚህ ጥናት በመስክ መረጃ የመሰብሰብ ተግባራ ለማከናወን የዝግጅት ተግባር እየተከናወነ ይገኛል።