በከተማ የሴት ሥራ አጥነት ከወንድ በእጥፍ እንደሚበልጥ ተገለጸ

የ2010 ዓ.ም አገር አቀፍ የከተማ የሥራ አጥነት 19.1 በመቶ መሆኑን ዓመታዊ የከተሞች የሥራ ስምሪት ጥናት ውጤት ሪፖርት አመለከተ።

በከተማ ለሥራ ብቁ ከሆኑት 9,289,150 ዜጎች ውስጥ  4,798,506 ወንዶች፤ 4,490,644 ሴቶች ሲሆኑ ከዚህ ውስጥ 584,585 ወይም 12.2 በመቶ ወንዶችና 1,185,709 ወይም 26.4 በመቶ ሴቶች ሥራ አጥ ናቸው። በአጠቃላይ በአገሪቱ ከተሞች 1,770,294  ወይም  19.1 በመቶ ዜጎች ሥራ አጥ መሆናቸውን ከዓመታዊ የጥናት ውጤት ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል።

18,773,035 እንደሚሆን ከሚገመተው የከተማ ነዋሪዎች ውስጥ ዕድሜያቸው አሥርና ከዚያ በላይ የሆኑ ዜጎች ቁጥር 14,971,603 ሲሆን ለሥራ ብቁ (Total Active Population) ዜጎች ቁጥር 9,289,150 ለሥራ ብቁ ያልሆኑት (Economically not Active) ዜጎች ቁጥር 5,682,453 ያመለከተው የጥናት ወጤቱ ለዚህም እንደምክንያት የተጠቀሰው ትምህርት ላይ መሆን፣ የቤት ውስጥ ሥራ፣ ለአቅመ ሥራ አለመድረስ፣ ጤና ማጣት፣ እርጅናና ሌሎች መሆኑን ጥናቱ አመላክቷል።

የሥራ አጥነት ሁኔታው ከክልሎችና ከተማ መስተዳድር አንፃር ሲታይ የድሬደዋ ከተማ  25.3፣ የትግራይ ክልል 21.5፣ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር 20.2፣  የአማራ ክልል 19.7 በመቶ እንዲሁም ቀሪ ክልሎች ከ10 – 19 በመቶ የሥራ አጥነት ምጣኔ ድርሻ ያስመዘገቡ ሲሆን  የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 8,971 በቁጥር ወይም 7.2 በመቶ በአንፃራዊነት አነስተኛውን የሥራ አጥነት ምጣኔ ድርሻ አስመዝግቧል።

በአገሪቱ በከተማ ዕድሜያቸው አሥርና ከዚያ በላይ ሆኖ በሥራ ላይ የተሰማሩ ዜጎች በአጠቃላይ 7,518,855 ሲሆኑ 4,213,920 ወይም 56 በመቶ ወንዶች፤ 3,304,935 ወይም 44 በመቶ ሴቶች እንደሆኑ ከጥናቱ ሪፖርት መረዳት ተችሏል።

በአገሪቱ ከተሞች ከተመዘገቡት 1,770,294 ሥራ አጦች ውስጥ 54 በመቶ የሚሆኑት በግል የራሳቸውን ሥራ ለመሥራት ቢያስቡም የገንዘብ እጥረት እንዳለባቸው፤ 10.3 በመቶ የሚሆኑት የሥራ ቦታ እጥረት እንዲሁም 5.3 በመቶ ለሥራ የሚያስፈልጋቸውን ሥልጠና እንዲሰጣቸው ቢፈልጉም አለማግኘታቸው ተግዳሮት እንደሆነባቸው የጥናቱ ውጤት ያመለክታል።

በጥናቱ በአፋር ክልል ሦስትና በሶማሌ ክልል ስድስት ዞኖች በስተቀር በሁሉም ክልሎችና በሁለቱ የከተማ መስተዳድሮች በ102 የቆጠራ ቦታዎች ውስጥ የሚገኙ 19,384 ቤተሰቦች በናሙና ተመርጠው መረጃዎቹ ተሰብስበዋል።

ከጥናቱ የተገኙት መረጃዎች ለሁሉም ተጠቃሚዎች ለማድረስ በሚያስችል መልኩ በማዘጋጀት በተቋሙ ቤተመጻሕፍት፣ በሥርጭት ቡድንና ሽያጭ ክፍል በሀርድ ኮፒ እንዲሁም በአዲሱ የተቋሙ ድረ ገጽ www.statsethiopia.gov.et ላይ በሚፈልጉት ፎርማት ፈልገው ማግኘት እንደሚችሉ ተገልጿል።