የ2012ዓ.ም የመስኖ እርሻ ናሙና ጥናትን ለማካሄድ የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ዝግጅቱን አጠናቋል

የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ የ2012ዓ.ም የመስኖ እርሻ ናሙና ጥናትን ለማካሄድ ከመጋቢት 02-10/2012 ዓ.ም በሁሉም ስታቲስቲክሰ ቅ/ጽ/ቤቶች ለ850 መረጃ ሰብሳቢዎችና ተቆጣጣሪዎች እንዲሁም ለ28 ስታቲስቲሺያኖች ስልጠና ሰጠ፡፡

መስኖ የሀገራችንን የግብርና ምርት ለማሳደግ ብሎም በአሁኑ ወቅት ከህዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ በከፍተኛ መጠን እየናረ የመጣውን የምግብ ፍላጎት ክፍተትን ለማሟላት ከፍተኛ ሚናን ይጫወታል፡፡ የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ በ2012 ዓ.ም የበጋ ምርት ወቅት በሀገሪቱ በሚገኙ የገጠር ቀበሌዎች፣ወረዳዎች፣ ዞኖችና ክልሎች የሚከናወነውን የመስኖ እርሻ ልማት ናሙና ጥናትን ለአምስተኛ ጊዜ ያካሂዳል፡፡ በመስክ ላይ የመረጃ አሰባሰብ ሙሉ በሙሉ ታብሌትን በመጠቀም የሚከናወን ሲሆን ይህም የመረጃ ጥራትንና ወቀወታዊነትን በመጨመር፤ ለጥናቱ የሚወጣውን ወጪ ከመቀነስ አንጻር የጎላ ሚና አለው፡፡ ጥናቱ የሚካሄደውም ወካይ ከሆኑና በሳይንሳዊ መንገድ ከመላ ሀገሪቱ በተመረጡ 1699 ቀበሌዎች ከሚገኙ በዘንድሮው በጋ ወቅት መስኖን ከተጠቀሙ ባለይዞታ አርሶአደር ላይ ነው፡፡

በጥናቱ በመስኖ እርሻ የተሸፈነ የመሬት ስፋት፣ በመስኖ ከለማው የመሬት ስፋት ላይ የተመረተውን ጠቅላላ ምርት፣ በመስኖ ከሚለማው ማሳ ላይ የሚገኘውን ምርታማነት በሰብል አይነት በሀገር አቀፍ፣ በክልልና በዞን ለይቶ ለማወቅ፤ የመስኖ እርሻ ሥራ አጠቃላይ ሁኔታን፣ በጥቅም ላይ የዋለ የማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘር፣ የአካባቢ ዘር፣ የፀረ-ሰብል መድኃኒትን እንዲሁም የመስኖ ተጠቃሚ ቤተሰቦች ለመስኖ የሚጠቀሙት የውሃ ምንጭን የተመለከቱ ዝርዝር መረጃዎች ይሰበሰባሉ፡፡

ለጥናቱ መረጃዎች በመስክ ከመጋቢት16 – ሚያዝያ 30/2012 የሚሰበሰብ ሲሆን ሪፖርቱ ግንቦት 30/2012 ዓ.ም ይፋ እንደሚደረግ ይጠበቃል፡፡ የጥናቱን ውጤት በዋናነት መንግስት የሚጠቀምበት ሲሆን፤ ለኢንቬስተሮችና ለተመራማሪዎች በመስኖ የለማ መሬትና የምርት መጠኑን በማወቅ ለሚፈልጉት መረጃ ለመጠቀም፤ በመስኖ አጠቃቀም ዙሪያ ለሚደረጉ ምርምሮች ጥናቶችን ለማከናወንና  እንደመነሻ ግብአትነት ያገለግላል፡፡