4ተኛውን ዙር ልማታዊ የምግብ ዋስትና ጥናት ለማካሄድ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት እየተከናወኑ ነው

የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ የ2013ዓ.ም አራተኛ ዙር ልማታዊ የምግብ ዋስትና ጥናትን ለማካሄድ ከመጋቢት 13/2013ዓ.ም ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ ሳምንታት የሚቀጥል ስልጠና በወላይታ ሶዶ፣ አርባ ምንጭ፣ ድሬዳዋና ደብረታቦር በሚገኙ ማዕከላት ለ885 መረጃ ሰብሳቢዎች፣ለ155 ተቆጣጣሪዎችና ለ57 ስታቲስቲሺያኖች ስልጠና በመስጠት ላይ ነው፡፡

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢራቱ ይገዙ  በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለጹት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የምግብ ዋስትና ችግር ለማቃለል መንግስት የተለያዩ ፕሮግራሞችን በመንደፍ ትግበራ ላይ የሚገኝ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ልማታዊ ሴፍቲኔት መርሀግብር አንዱ ነው፡፡

የልማታዊ ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ጥናት ከዚህ ቀደም በ3ዙር የተጠና ሲሆን ለ4ተኛ ጊዜ የሚካሄደው ጥናት አላማ በሀገራችን በደጋ፣ በቆላና በአርብቶ አደር አካባቢዎች ሲተገበሩ የቆዩት ፕሮግራሞች የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ አንፃር የታዩትን ለውጦች የስታቲስቲክስ መረጃን መሰረት በማድረግ ለመገምገምና እንዲሁም ለቀጣይ አምስት አመት ተመሳሳይ ፕሮግራም ዕቅድ መነሻ በመሆን የሚያገለግል መረጃ መስጠት እንደሆነ ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡   

ልማታዊ የምግብ ዋስትና ጥናት የሚካሄደው ወካይ ከሆኑና በሳይንሳዊ መንገድ ከመላ ሀገሪቱ በተመረጡ 13,682 የሴፍቲኔት ተጠቃሚ ቤተሰቦች ነው፡፡

በመስክ መረጃ የመሰብሰቡ ተግባር በታብሌት ቴክኖሎጂ የታገዘ ሲሆን በሥራ ለሚሰማሩት ሁሉም ባለሞያዎች ለ21 ቀናት የሚቆይ ስልጠና በተለያዩ አራት ማዕከላት እየተሰጠ ይገኛል፡፡ ተቋሙ በሁሉም ደረጃ የሚያከናውናቸው ተግባራት ኮቪድ-19 ቫይረስን ለመከላከል የሚያስፈልጉትን ግብአቶች በማሟላትና ተግባራዊ በማድረግ እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል፡፡