ሥነ-ምግባራዊ አመራርና የስራ ሥነ-ምግባር ላይ ያተኮረ ስልጠና ተሰጠ

ሥነ-ምግባራዊ አመራርና የስራ ሥነ-ምግባር ላይ ያተኮረ ስልጠና ከጥር 23-27/2014ዓ.ም በአዳማ ድሬ ኢንተርናሽናል ሆቴል ከፕላን ሚኒስቴርና ከተጠሪ ተቋማት ለተውጣጡ አመራሮችና ከፍተኛ ባለሙያዎች ስልጠና ተሰጠ።

የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሳፊ ገመዲ መድረኩን በንግግር የከፈቱ ሲሆን በአለም ላይና በሀገራችን ለሰው ልጆች ፍትህ ማጣት፣ ፍትሀዊነት መጓደልና ለዲሞክራሲያዊ ዕድገት መቀጨጭ ዋና ዋና ከሚባሉት ችግሮች መካከል የመልካም ሥነ-ምግባር ውድቀትና ሙስና መሆኑን ገልፀዋል። በሀገራችን ላይ ሙስና በከፍተኛ ሁኔታ እተስፋፋ መሆኑንና ከፍተኛ ቀውስ እያስከተለ መሆኑን ገልፀው ይህም በመንግስትና በዜጎች መካከል አለመተማመን በመፍጠር ለከፋ ችግር እንደሚዳርግ ተናግረዋል።

ይህንን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት በተቋሙ የሚገኘው የሥነ-ምግባርና ሙስና መከላከል ዳይሬክቶሬት በተቋሙ ለሚገኙ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም አዲስ ለሚሾሙ፣ ለሚመደቡና ለሚቀጠሩ ሀላፊዎችና ሰራተኞች  በሥነ-ምግባር ግንባታና በሙስና መከላከል ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በመስጠት የተሰጠውን ሀላፊነት በመረዳት በትኩረት እየሰራበት እንደሆነ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

በስልጠናው ላይ ስለሥነ-ምግባራዊ አመራር፣ ስለስራ ሥነምግባር፣ ስለጥቅም ግጭትና ስለመልካም አስተዳደር ከፌዴራል ሥነምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን በመጡ አሰልጣኞች በሰፊው ገለፃ የተደረገ ሲሆን የተለያዩ የመወያያ ርዕሶችን በማንሳት በስራ ላይ የሚታዩ ችግሮች ላይ በቡድን ውይይት ተደርጓል። ስልጠናው ከፕላን ሚኒስተር፣ከኢትዮጰያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት፣ከፖሊሲ ጥናትና ኢንስቲትዩትና ከአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ለተውጣጡ 50 ለሚሆኑ የስራ ሀላፊዎችና ከፍተኛ ባለሙያዎች ስልጠናው ተሰጥቷል።