የኤጀንሲውን ዓርማ የተመለከተ ዜና

ኤጀንሲው አዲስ ዓርማ ይፋ አደረገ

የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ እንደ ተቋም አሁን የደረሰበትንና ወደፊት የሚደርስበትን ተቋማዊ ዕይታ የሚወክል አዲስ ዓርማ ይፋ አድርጓል።

ኤጀንሲው ይፋ ያደረገው አዲስ ዓርማና ብራንዲንግ ከዚህ በፊት ለረጅም ጊዜያት ሲጠቀምበት የነበረውን ዓርማ የሚተካ ሲሆን ከተቋማዊ ተልዕኮ አፈጻጸም አንፃር አሁን የደረሰበትን አቅምና ወደፊት የሚደርስበትን ደረጃ መወከል የሚችል ሆኖ ተዘጋጅቷል።

ኤጀንሲው ከተቋቋመበት ከ1952 ዓ.ም ጀምሮ መረጃዎችን በወረቀት በመሰብሰብና በመተንተን ሲያሰራጭ የቆየ ሲሆን በየጊዜው ባደረጋቸው ተቋማዊ የአቅም ግንባታ በአሁኑ ወቅት  መረጃዎችን ከመስክ መሰብሰብ እስከ ለተጠቃሚዎች ማቅረብ ያለው ሂደት በታብሌት ቴክኖሎጂና በጂፒኤስ እየታገዘ በማከናወን ላይ ይገኛል። ስለሆነም የቀድሞው ዓርማ /Logo/ ኤጀንሲው በመረጃ መሰብሰብ እና ማጠናቀር እንዲሁም ማሰራጨት ላይ ያመጣውን የአሰራር ለውጥ በበቂ መልኩ የማያመላክት ከመሆኑ በተጨማሪ ዲጂታል ሚዲያዎችን ፎርማት ለመጠቀም የሚያመች አዲስ ዓርማ እንደሚያስፈልገው ታምኖበት አዲሱ ዓርማ ተዘጋጅቷል።

በሌላ በኩልም ለመላው ህብረተሰብ በተሻለ ዕይታ ተቋሙን ለማስተዋወቅና ተከታታይ የኮሙዩኒኬሽን ሥራ ለመስራትና ከዘመኑ ጋር መራመድ የሚችል የተቋሙን ተልዕኮ የሚወክል አዲስ ዓርማ ማዘጋጀት ሌላኛው ምክንያት ሆኖ ተገኝቷል።

በዚሁ መነሻ መስከረም 12 እና 13 ቀን 2012 ዓ.ም በተካሄደው አገር አቀፍ የስታቲስቲክስ መረጃ ሥርጭትና የስታቲስቲክስ ለውጤት ፕሮጀክት የመዝጊያ ወርክሾፕ ላይ አዲስ ዓርማ /Logo/ ቀርቦ ለህብረተሰቡ የማስተዋወቅ ሥራ የጸጀመረ ሲሆን በቀጣይ ኤጀንሲው በሁሉም እንቅስቃሴዎቹና የግንኙነት ሥራዎቹ ላይ ተቋሙን የሚወክለው አዲሱ ዓርማ ይሆናል። ተቋሙ ባለው ተንቀሳቃሽና ቋሚ ንብረቶች ላይ በሙሉ ዓርማው ተግባራዊ እንደሚደረግ ተገልጿል።

አዲሱ ዓርማ የተዘጋጀው ከነብራንዲንጉ በመሆኑ በተቋሙ ውስጥ የሚነበቡና የሚፃፉ እንዲሁም ተቋሙ በማህበራዊ ሚዲያ እንዲሁም ለህትመትም ሆነ ለኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች የሚላኩት ግብአቶችና የሚዘጋጁ የጥናቶች ሪፖርትና መጽሔቶች በሙሉ ብራንዲንጉ ያስቀመጣቸውን መስፈርቶች አሟልተው የሚታተሙ ስለመሆናቸው ተጠቁሟል።

በመሆኑም ከዚህ በኋላ ከተቋሙ ጋር የሚሰሩ ባለድርሻ አካላት፣ የተቋሙ የዋና መ/ቤት የሥራ ክፍሎችና ቅ/ጽ/ቤቶች ተቋሙን የሚገልፀው የቀድሞ ዓርማ በአዲስ ዓርማ መተካቱን ከግንዛቤ በማስገባት ሊሰሩበት እንደሚገባ ኤጀንሲው አስታውቋል። ከዚህ ጋር ተያይዞ የተቋሙ የግንኙነት መሳሪያዎች እንደ ሄደር ፔፐር እና ማህተም በአዲሱ የመተካት ሥራዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ተሰርተው እንደሚጠናቀቁ ተጠቁሟል።

በአጠቃላይ የዚህ አዲስ ዓርማ አስፈላጊነትና ምንነት ላይ በተገቢው መልኩ ግንዛቤ ተወስዶ ተግባራዊ ማድረጉ ላይ ሁሉም አካል የበኩሉን እንዲወጣ ኤጀንሲው ጥሪውን አስተላልፏል።