በትላልቅ፣መካከለኛ፣ጥቃቅንና አነስተኛ ማምረቻ ኢንዱስትሪ ጥናት ለሚሳተፉ መረጃ ሰብሳቢዎች ስልጠና ተሰጠ

የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የትላልቅ፣መካከለኛ፣ጥቃቅንና አነስተኛ ማምረቻ ኢንዱስትሪ ጥናት ከየካቲት 7 እስከ 12/2014ዓ.ም በአዳማ፣ በሀዋሳ፣ በጅማ፣በድሬዳዋ፣በሶዶና ደብረታቦር የስልጠና ማዕከላት ለመረጃ ሰብሳቢዎች ስልጠና ተሰጠ።

የተቋሙ የኮሙየኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሳፊ ገመዲ መድረኩን በንግግር የከፈቱ ሲሆን  የትላልቅ፣መካከለኛ፣ጥቃቅንና አነስተኛ ማምረቻ ኢንዱስትሪ ጥናት ለሀገሪቷ ፖሊሲ ቀረፃና እቅድ ለማውጣት የሚጠቅም ወሳኝ መረጃ መሆኑን ገልፀው መረጃ ሰብሳቢዎች ወደማምረቻ ድርጅቶች በሚሄዱበት ጊዜ ስለጥናቱ ጠቀሜታና አስፈላጊነት በመግለፅና ግንዛቤ በመፍጠር ትክክለኛና ጥራት ያለው መረጃ እንዲሰበስቡ አሳስበዋል።

የዚህ ጥናት ዓላማ በዘርፉ የተሰማራውን የሰው ሀይል መረጃ ለማግኘት፣ የማምረቻ ኢንዱስትሪ ዘርፉ ያሉበትን ችግሮች ለማወቅና መፍትሄ ለመፈለግ፣ በዘርፉ የሚታየውን የስታቲስቲክስ መረጃ ክፍተት ለማሟላት፣የማምረቻ ዘርፉ ከሌላው የኢኮኖሚ ዘርፍ ጋር በተለይም ከግብርና ጋር ያለውን ግንኙነት ለማወቅ እንደሆነ በስልጠናው ተገልጿል።

በዚህ ጥናት የማምረቻ ድርጅቱ ወይም የአገልግሎት ሰጪው ድርጅት መሰረታዊ መረጃዎች፣ በስራው የተሰማራውን የሰው ሀይል፣ ደምወዝና ምንዳ በሙያ፣ መደብ፣ፆታና የምርት ዓይነት፣ የምርት ሽያጭ፣ ሌሎች ልዩ ልዩ ገቢዎችና ክምችት ፣ ድርጅቱ ስለተጠቀመባቸው ጥሬ እቃዎች ወጪና ሌሎች ወጪዎች፣ ስለድርጅቱ ቋሚ ንብረትና መዋዕለ ንዋይ ሁኔታ፣ የማምረት አቅም፣ የተያያዙ ችግሮችና የድርጅቱ ሰራተኞች ዋና ዋና የስነ-ሕዝብ ባህሪያት ከጥናቱ የሚገኙ ዋና ዋና መረጃዎች ናቸው።

በዚህ ስልጠና ለትላልቅና መካከለኛ ማምረቻ ኢንዱስትሪ ጥናት 153 ለሚሆኑና ለአነስተኛና ጥቃቅን ማምረቻ ኢንዲስትሪ ጥናት 634 ለሚሆኑ በአጠቃላይ 787 ለሚሆኑ መረጃ ሰብሳቢዎች ስልጠናው ተሰጥቷል።