በጦርነቱ ለተጎዱ ዜጎች የተሰሩ ቤቶች የቁልፍ ርክክብ ተደረገ

ሐምሌ 23/2015ዓ.ም አፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ዞን አንድ አዳር ወረዳ ካሳ ጊታ ከተማ፤ በጦርነቱ ቤታቸው ለወደመባቸው አስር አባውራዎች በ2014ዓ.ም የክረምት በጎ አድራጎት ፕሮግራም በፕላንና ልማት ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት የተገነቡ አስር ቤቶችን የክልሉ ፕሬዝደንትና የአራቱ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ለተጎጂዎች የቁልፍ ርክክብ ስነ-ስርዓት ተከናወነ።

ባለፈው ዓመት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የተካሄደው አውዳሚ ጦርነት በተካሄደበት ታሪካዊ የካሳጊታ ከተማ ‘‘ካሳ ጊታን መገንባት ኢትዮጵያዊነትን መገንባት ነው’’ በሚል መሪ ቃል ፕላንና ልማት ሚኒስቴርና ሶስቱ ተጠሪ ተቋማት ከሰባት ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ጉዳት ከደረሰባቸው አባውራዎች መካከል ምንም አቅም ለሌላቸው አባውራዎች የተገነቡ ቤቶች የቁልፍ ርክክብ ተደርጓል። በርክክብ ፕሮግራሙ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የክልሉ ፕሬዝደንት አቶ አወል አርባ ጠላት የሀገሪቱ ጉሮሮ የሆነችውን ሚሌን በመያዝ ሀገሪቷን ለመጉዳት ባደረገው ተደጋጋሚ ጥቃት በተደረገባት ካሳጊታና አካባቢዋ ያለውን ህዝባችን የከፈለው ውድ መስዋዕትነት ለእኛ ነው ብላችሁ በማሰብ ለተጎዱ ወገኖቻችሁ የገነባችሁት ቤቶች ለክልሉ መንግስትና ህዝብ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠውና ምስጋና የሚገባው ተግባር በመሆኑ ለፕላንና ልማት ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት አመራሮችና ሰራተኞች ከፍተኛ ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን ይህ አካባቢ አሁንም ብዙ ድጋፍ የሚጠይቅ በመሆኑ ሌሎችም ይህን ሞዴል ተግባር በማየት የበለጠ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

በዕለቱ የፕላንና ልማት ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማትን በመወከል የቁልፍ ርክክብ መልዕክት ያስተላለፉት የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ሚኒስተር ዴኤታ ወ/ሮ ጥሩማር አባተ ባለፈው ዓመት የአረንጓዴ አሻራና የበጎ አድራጎት ተግባራት ለማከናወን በክልሉ አዳር ወረዳ ስንመደብ ወቅቱ ጦርነቱ ያደረሰው ውድመት አሻራ በግልፅ የሚታይና የካሳጊታ ከተማ ነዋሪዎች ቤቶቻቸው ወድሞ ሜዳ ላይ የሚገኙበት ጊዜ በመሆኑ ችግኝ የመትከልና ሌሎች ድጋፎችን አድርገን መመለስ ብቻ ለዚህ ታላቅ ተጋድሎ ለፈፀመ ህዝባችን በቂ አይደለም በማለት ሁሉንም ችግር በአንዴ መፍታት ባንችልም አስር የሚሆኑ አባውራዎችን ከፀሀይ ወደ ጥላ እናስገባቸው በሚል አስር ቤቶችን ገንብተን ለማስረከብ የገባነውን ቃል ተግባራዊ ሆኖ በማየታቸው ታላቅ ኩራት እንደተሰማቸው ገልፀው ቤት ለተገነባላቸው አባውራዎች እንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት በማስተላለፍ ይህ ተግባር እንዲሳካ አስፈላጊውን ድጋፍ ላደረጉት የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ፣ የወረዳው አመራር እንዲሁም ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለተመደቡ ኮሚቴዎች ምስጋና አቅርበዋል።

በቁልፍ ርክክቡ ስነ-ስርዓት ላይ የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና ተጠሪ ተቋማት ላደረጉት ድጋፍ የእውቅና ሽልማት በክልሉ ፕሬዝደንት እጅ አበርክተዋል።