የስርዓተ-ፆታ ስታቲስቲክስን በሁሉም ጥናቶች ውስጥ ለማካተት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

የስርዓተ-ፆታ ስታቲስቲክስን በሁሉም ጥናቶች ውስጥ ለማካተት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ስርዓተ-ፆታን በስታቲስቲክስ ውስጥ ለማካተት ተግባራዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መሆኑ ተጠቆመ፡፡ ይህ የተጠቆመው ኤጀንሲው እና UN-WOMAEN በጋራ በመተባበር ለኮሚኒኬሽን እና ስርዓተ- ፆታ ባለሞያዎች ስለ ስታቲስቲክስ እና ስርዓተ-ፆታ መረጃ ግንዛቤ ለማሳደግ በጋራ ባዘጋጁት የስልጠና መድረክ ላይ ነው፡፡

የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወ/ት አበራሽ ታሪኩ ስልጠናውን በንግግር በከፈቱበት ወቅት ስርዓተ-ፆታ ስታቲስቲክስን በሁሉም ስታቲስቲክስ ጥናቶች ውስጥ አካቶ ለማጥናት ኤጀንሲው የአምስት አመት እቅድ ነድፎ እየሰራ እንደሆነ እና በቀጣይም የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው ስርዓተ-ፆታ በሁሉም ስታቲስቲክስ ውስጥ መካተቱም ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው አያይዘው አስታውቀዋል፡፡

ስርዓተ-ፆታ ተኮር መረጃዎች ሀገራዊ የልማት ትልሞች እና የሚሊኒየም ግቦችን ለማሳካት በማህበራዊ፤ በኢኮኖሚያዊና ዲሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ውስጥ የጾታ እኩልነትን ለማረጋገጥ በሚታቀዱ እቅዶችና ፖሊሲዎች በግብአትነት፤ ለክትትልና ግምገማ ያላቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ስለመሆኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ አስረድተዋል፡፡ ከዚህ አንጻር የማከላዊ ስታቲስቲክስ ድርሻ የጎላ ቢሆንም ሁሉም ሴክተር መስሪያ ቤቶች ከራሳቸው አስተዳደራዊ መዛግብት ስርዓተ-ፆታ ተኮር መረጃዎች በማመንጨት ለፖሊሲ ቀረጻና ለውሳኔ አሰጣጥ ለመጠቀም መስራት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡

በስልጠና መድረኩ በስርዓተ ፆታ ዙሪያ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎች የቀረቡ ሲሆን የማእከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ የማመንጨት እና የማሰራጨት ተግባር እና ሀላፊነት፣ የስርዓተ-ፆታ ጽንሰ ሀሳብ፣ የስርዓተ-ፆታ ስታቲስቲክስ ምንነት እና አስፈላጊነት፣ ስርዓተ ፆታ ስታቲስቲክስ መረጃ በብሄራዊ የስታቲስቲክስ ስርአት ውስጥ ማካተት እና የስታቲስቲክስ መረጃ ስርጭት ሂደት እና የድህረ ገፅ አጠቃቀም የተመለከቱ ርዕሰ ጉዳዮች በስፋት ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

በመጨረሻም በስልጠናው መዝጊያ ተሳታፊዎች ተሞክሯቸውን ያካፈሉ ሲሆን ኤጀንሲው የሚያካሂዳቸው ጥናቶች ስርዓተ-ፆታን ያማከለ እንዲሆን እና ሌሎች ጥሩ ግብአት የሚሆኑ ሀሳቦችን ካቀረቡ በኋላ ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ ሁሉም ሴክተር መስሪያ ቤቶች ስርዓተ-ፆታን በስተቲስቲክስ ጥናቶች ውስጥ በማካተት የበኩላቸውን ተሳትፎ እንዲያደርጉ በማሳሰብ ስልጠናውን ዘግተዋል፡፡

ከተለያዩ ሴክተር መስሪያቤቶች እና ከማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ የተወጣጡ 40 የዘርፉ ባለሞያዎች ከህዳር 22-23/2012ዓ.ም በአዳማ ራስ ሆቴል በተሰጠው ስልጠና ላይ ተሳትፈዋል፡፡