የተቋሙ ሰራተኞችና አመራሮች የአለም የሴቶች ቀንን በጋራ አከበሩ

በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ለ111ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ለ46ኛ ጊዜ የሚከበረውን የዓለም የሴቶች ቀን ‹‹እኔም ለእህቴ ጠባቂ ነኝ›› በሚል መሪ ቃል የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት አመራርና ሠራተኞች በጋራ በመሆን በተቋሙ የስብሰባ አዳራሽ መጋቢት 02/2014ዓ.ም አክብረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳ/ር አቶ ቢራቱ ይገዙ መድረኩን በንግግር  የከፈቱ ሲሆን በንግግራቸው በዓሉ በሴቶች እኩልነት ረገድ የተገኙ ድሎችን ለማስታወስና ለማስጠበቅ እንዲሁም የሴቶች እኩልነት በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮችን ለማረጋገጥ የሚውልና ወንዶች ከሴቶች ጋር የጋራ አንድነታችንን የምናሳይበት ቀን  ነው ብለዋል፡፡ በዓሉ የዓለም ሴቶች ለመብታቸው መከበር ያደረጉትን ትግል የሚያሳይ፣ በሴቶች በኩል የታዩ መሻሻሎች የሚንጸባረቁበትና ለሴቶች ብርታትና ቁርጠኝነት ዕውቅና የሚሰጠበት ዕለት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሴቶችን ዕኩልነት ከጎናቸው በመቆም ማረጋገጥ አለብን ያሉት ዋና ዳ/ሩ ትግበራውን የምናሳይበትና ለአላማው ቃል የምንገባበት ቀን እንደሆነና ሴቶችን ማብቃትና ወደአመራር ደረጃ ማምጣት  የሴቶች ብቻ ሳይሆን የወንዶች ሀላፊነትም እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በዓሉ በሴቶች እኩልነት ረገድ የተገኙ ድሎችን ለማስታወስና ለማስጠበቅ እንዲሁም ያልተፈቱ ችግሮችን ለመፍታት ሴቶች የሚታገሉበት መድረክ እንደሆነ በዕለቱ ተነገሯል፡፡ የዘንድሮውን አለምአቀፍ የሴቶች ቀን ለተጎዱ ሴቶችና ህጻናት ድጋፍ በማድረግና የተሻለ አፈጻጸም ያላቸውን እውቅና በመስጠት እስከመጋቢት 18/2014ንቅናቄው እንደሚቀጥል ከመድረኩ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በመጨረሻም የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ሠራተኞች  በሴቶች ጉዳይ  በቀጣይ መሰራት ስላለባቸው ስራዎች ውይይት ተደርጎ ክብረ በዓሉ ተጠናቋል።