የወሳኝ ኩነት ምዝገባ እና የቫይታል ስታቲስቲክስ ስርዓት ላይ ስልጠና ተሰጠ

የወሳኝ ኩነት ምዝገባ እና የቫይታል ስታቲስቲክስ ስርዓት ላይ ስልጠና ተሰጠ

በወሳኝ ኩነቶችና ምዝገባና የቫይታል ስታቲስቲክስ ስርዓቶች በሚል መነሻ ሀሳብ ላይ በአዳማ ደምበል ቪው ሆቴል ከህዳር 21 አስከ ህዳር 25/2013 ዓ.ም ስልጠና ተሰጠ።

በስልጠናው መክፈቻ ላይ ተገኝተው ስልጠናውን በንግግር የከፈቱት የኤጀንሲው የስነ-ሕዝብና ቫይታል ስታቲስቲክስ ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ አሳልፈው አበራ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ለቫይታል ስታቲስቲክስ ያለውን ጠቀሜታ በመግለፅ ማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ከኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ጋር ባደረጉት ስምምነት መሰረት ማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ አንድ ኮፒ በመቀበል ለስታቲስክስ ስራ የሚውሉትን መረጃዎች በመለየትና በመጠቀም፣ በማጠናቀር ለተጠቃሚዎች ሪፖርት ለማውጣት እየሰራ ይገኛል ሲሉ ገልፀዋል። በቀጣይ ሁሉም ህብረተሰብ ስለመረጃው ጠቀሜታ ግንዛቤ አግኝቶ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ በወቅቱ እንዲያካሂድ ሁሉም ሰራተኛ የሚያውቀውን የማስገንዘብና የቅስቀሳ ስራ መስራት አለበት ሲሉ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ  በዋናነት የወሳኝ ኩነት ምዝገባ የሚካሄድባቸው ኩነቶች ልደት፣ ጋብቻ፣ ፍቺና ሞት ሲሆኑ በስልጠናው ላይ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ስርዓት ትርጉም፣የሚያስገኛቸው ጥቅሞች፣ የሚመዘገቡት መረጃዎች፣ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ስርዓት ምንነት፣ በወሳኝ ኩነት የሚካተቱ የመረጃ አይነቶች፣ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ አስፈላጊነትና ጠቀሜታ ላይ ትኩረቱን ያደረገ ስልጠና ተሰጥቷል። ከወሳኝ ኩነት ምዝገባ የሚገኘው የቫይታል ስታቲስቲክስ መረጃዎች ያላቸው ጠቀሜታዎች የህዝብ ቁጥርን ለመተንበይ፣ የልደትና የሞት መጠን መረጃዎችን ለማግኘት፣ ለሞት መንስኤ የሆኑ ምክንያቶችን መረጃ ለማግኘትና የጋብቻና የፍቺ መጠን መረጃ ለማግኘት ይጠቅማል።

ከስልጠናው ተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የተነሱ ሲሆን የስነ-ሕዝብና ቫይታል ስታቲስቲክስ ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ አሳልፈው አበራ በስልጠናው መዝጊያ ላይ ይህ ስራ የኤጀንሲው ዋነኛ  ተግባር መሆኑን ተገንዝቦ መሰራት አለበት ሲሉ ተናግረዋል። ስራው የተለያዩ ችግሮች ያሉበት ሲሆን በዋናነት የጊዜና መረጃዎች በትክክል ፎርሙ ላይ ያለመሞላት ችግሮች ዋነኛ ናቸው ብለዋል። ችግሮቹን ለመቅረፍም መረጃው የሚሰበሰብበትን መንገድ ዲጂታል ለማድረግ እየተሞከረ ነው ሲሉ ገልፀዋል። ኤጀንሲው ማሟላት ያለበትን ለስራው የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን እንደሚያሟላ ገልፀው በቀጣይም በዚህ ስልጠና የተሳተፉ ባለሙያዎች በሚመደቡበት ስራ የሚጠበቅባቸውን ስራ መስራት አለባቸው ሲሉ ተናግረዋል።

ስልጠናው ከዋናው መ/ቤትና ቅ/ጽ/ቤቶች ለተውጣጡ 55 የዳታ ኢንትሪ፣ ዳታ ክሊኒንግ፣ ኤዲተሮችና የዶክመንቴሽን ባለሙያዎች ስልጠናው ተሰጥቷል። በስልጠናው የተሳተፉት ባለሙያዎችም በቂ ግንዛቤ ማግኘታቸውንም ገልፀዋል።