በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ከተጠሪ ተቋማት ጋር ውይይት አካሄዱ

የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ከተጠሪ ተቋማት ጋር በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የመንግስት ሰራተኛው ስለሚኖረው ሚና ህዳር1/2014ዓ.ም በማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ የስብሰባ አዳራሽ ውይይት አካሄዱ፡፡

 የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር የሆኑት ሚኒስትር ዶክተር ፍፁም አሰፋ ውይይቱን በንግግር የከፈቱት ሲሆን በንግግራቸውም እያንዳነዱ ሰራተኛ የተሰጠውን ስልጣንና ሃላፊነት በታማኝነትና በአግባቡ በመወጣት እንደወታደር ዝግጁ መሆን እንዳለበት አስረድተው የተሳሳተ መረጃን በማህበራዊ ድህረ ገጽ ባለማሰራጨት ሀገራችን እንድታሸንፍ  ሰራተኛው የበኩሉን እንዲወጣ ገልጸዋል፡፡

በዕለቱ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የጽህፈት ቤት ሀላፊ የሆኑት አቶ ገረመው ነጋሳ ለውይይት መነሻ የሚሆኑ ሃሳቦችን ያቀረቡ ሲሆን ባለፉት ሦስት ዓመታት በኢትዮጵያ የነበሩ እድሎችና ያጋጠሙ ፈተናዎች ላይ ዳሰሳ ተደርጓል። 

በመጨረሻም የፕላንና ልማት ሚኒስቴር የፕላን ስታቲስቲክስ እና ፖሊሲ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ነመራ ገበየሁ እና የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢራቱ ይገዙ አወያይነት ከሠራተኞች ጋር በቀጣይ መሰራት ስላለባቸው ስራዎች ውይይት ተደርጎ መድረኩ ተጠናቋል።