በሀገራዊው የለውጥ ሂደት ሰራተኛው የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ

መመድረኩንዊ ስታቲስቲክስ አመራሮች እና ሠራተኞች ሀገራዊው የለውጥ ሂደት እንዲሳካ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ፡፡ ጥሪው የቀረበው የለውጡ ሂደት እና የሠራተኛው ሚና በሚል ርዕሰ ጉዳይ ላይ ታህሳስ 07/2012 ዓ.ም የኤጀንሲው ሰራተኞች እና አመራሮች ባካሄዱት የውይይት መድረክ ላይ ሲሆን የፕላን ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ መድረኩን ሲከፍቱ እንዳስታወቁት ሀገራችን የተያያዘችውን የለውጥ ሂደት በማስቀጠል ረገድ ሲቪል ሰርቫንቱ የማይተካ ሚናውን ሊጫወት ይገባል ሲሉ ገለጹ፡፡

ኢትዮጵያ ባለፉት15 አመታት በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ መስኮች አዎንታዊ ለውጦችን እንዳስመዘገበች አያይዘው ያብራሩት ምክትል ኮሚሽነሯ ለተከታታይ 14 አመታት ባለሁለት አሀዝ ዕድገት በማስመዝገቧ የድህነት ምጣኔ ከነበረበት 43 በመቶ ወደ 23 በመቶ እንደቀነሰ፣መሰረተ-ልማት እና ማህበራዊ አገልግሎትም እንዲዳረስ መሰራቱን አስታውቀዋል፡፡

በአንጻሩ ደግሞ በለው ጥሂደቱ የተደራጀ ሌብነት፣ የመልካም አስተዳደር ችግር፣ የዋጋ ግሽበት፣ የውጪ ምንዛሬ መናር፣ ከፍተኛ የሆነ የህዝብ እርካታ ጉድለት እንደአሉታዊ ተጽዕኖ መታየቱ እና ይህም ተጽዕኖ ገዢው ፓርቲ ወደ ጥልቅ ተሀድሶ እና ውህደት እንዲንደረደር ማድረጉን የገለጹት ኮሚሽነሯ በነበረው የፖለቲካ አስተሳሰብ እና አሰራር አሁን ህዝቡ የሚፈልገውን ለውጥ ለማምጣት ስለማይቻል የፓርቲው አመራር እና አባላት ሰፊ ውይይት በማድረግ አሁን ያለውን እና የወደፊት የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ማድረግ በሚያስችል አስተሳሰብ እና አሰራር የሚመራ አዲስ ውህድ ፓርቲ መፈጠር እንዳለበት ከመግባባት ላይ የተደረሰ ሲሆን በዚህም መነሻ ብልጽግና ፓርቲ መመስረቱን ገልጸዋል፡፡

ባለፉት አንድ አመት ተኩል ውስጥ ከነበሩት የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ተግዳሮቶች ለመውጣት በተደረገው እልህ አስጨራሽ ሂደት ምንም እንኳን ብዙ ፈታኝ ጉዳዮች ቢኖሩም ኢኮኖሚው በመረጋጋት፤ሀገር ውስጥ የፖለቲካ ምህዳሩን እንዲሰፋ፣በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና የነበረው የጠላትነት መንፈስ ተገፎ የትብብር መንፈስ እንዲደረጅ የተሰሩ ስራዎች ባለፉት ብዙ አመታት ለማሳካት ያልተቻሉ ብቻ ሳይሆኑ ይሆናሉ ተብለው ያልተገመቱ ድሎች የተገኙበት እና በዚህም ሀገራችን በአለም አቀፍ ሀገሮች እና ህዝቦች ዘንድ የነበራትን ዕይታ እንዲስተካከል ያደረጉ ስኬቶች እንደ ተመዘገቡ ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩልም ሁሉም ሴክተር መስሪያቤቶች እንደየተልኳቸው ለህዝቡ የተሻለ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሪፎርም እንዲያደርጉ አቅጣጫ ተሰጥቶ እየተሰራ ሲሆን ማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ አሁን መንግስት ለሚያስበው ምክንያታዊ፣ ፍትሀዊ፣ ተደራሽ እና ውጤታማ ልማት እና ዕቅድ የሚያስፈለጉትን መረጃዎች አሁን ካለበት በተሻለ ሁኔታ ለማቅረብ የሚያስችለውን ቁመናና አደረጃጀት እንዲሁም አሰራር እንዲኖረው የሚያስችል ሪፎርም እያደረገ እንደሚገኝ ለስኬታማነቱም ሁሉም የተቋሙ ሰራተኞች እንዲሳተፉ የየራሳቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለባቸው ኮሚሽነሯ በአፅንኦት አሳስበዋል፡፡

በመጨረሻም ከሰራተኞች የተለያዩ ሀሳብ እና ጥየቄዎች ተነስተው ኮሚሽነሯ ምላሽ ከሰጡ በኋላ ውይይቱ ተጠናቋል፡፡