የወሳኝ ኩነት ምዝገባና ቫይታል ስታቲቲክስ መረጃ አያያዝ ስርዓትን ዲጂታል ለማድረግ የሚያስችል ሰነድ ተፈረመ

የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲና የኢሚግሬሽን፣ ዜግነትና የወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ የወሳኝ ኩነት ምዝገባና ቫይታል ስታቲስቲክስ መረጃ አያያዝ ስርዓትን ዲጅታል ለማድረግ የሚያስችል ፕሮጀክት በጋራ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የስምምነት ሰነድ ጥቅምት 05/2014ዓ.ም በኢሚግሬሽን፣ ዜግነትና የወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ የስብሰባ አዳራሽ ተፈራረሙ፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ስርዓት አሁን እየተተገበረ ካለበት ወረቀት ላይ ከሚመዘገብበት አሰራር ታብሌቶች በመጠቀም ወደመመዝገብ አሰራር በመሸጋገር አጠቃላይ ስርዓቱን ዲጅታል በማድረግ ለሥራው የሚያስፈልገውን የሰው ሀይል፣ ጊዜና ገንዘብን በቁጠባ ለመጠቀምና መረጃዎችን በቀላሉ ወደ ማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ዳታ ቋት ለመላክ ይህ ፕሮጀክት ያለውን ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑን በመረዳት ለዚሁ ፕሮጀክት ተግባራዊነት ከሁለቱ ተቋማት የተቋቋመ የጋራ ኮሚቴ ጠንክሮ መስራት እንዳለበት በፊርማ ስርአቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢሚግሬሽን፣ ዜግነትና የወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙጂብ ጀማል ገልጸዋል፡፡

አሁን ባለው አሰራር በየክልሉ በምዝገባ ተሰብስበው ወደማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ የሚመጡ መረጃዎች በወረቀት ላይ የተመዘገቡ በመሆናቸው የሚይዙት ቦታና መረጃዎችን ወደ ኮምፒውተር በማስገባት የመጨረሻው ሪፖርት በአጭር ጊዜ ለተጠቃሚዎች ከመድረስ አንጻር ያለው ተፅዕኖ ከፍተና በመሆኑ ይህ ፕሮጀክት ያለውን ተፅዕኖ በሂደት በመቀነስ የሪፖርት ዝግጅት ስራን ለማቀላጠፍና በአጭር ጊዜ መረጃን ወደተጠቃሚዎች ለማድረስ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ ኤጀንሲው ለተግባራዊነቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢራቱ ይገዙ አስረድቷል፡፡ ፕሮጀክቱ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር እስከ ታህሳስ 30/2021ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን ለፕሮጀክቱ ተግባራዊነት የሚስፈልገው 470ሺህ ዶላር ከዓለም ባንክ ድጋፍ ተደርጓል፡፡ ፕሮጀክቱ በተመረጡት 1200 የምዝገባ ጣቢያዎች ላይ ተግባራዊ የሚደረግ እንደሆ ከተደረገው ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ፕሮጀክቱ የምዝገባ ስርዓቱን ታብሌት ቴክኖሎጂን በመጠቀም ፤በአምስት የተለያዩ ቋንቋዎች የወሳኝኩነት መረጃዎችን በመመዝገብና ዲጅታሊ ወደ ማዕከላዊ መረጃ ቋት መላክ የሚያችል የሰው ሃይል ስርዓትና አደረጃጀት አቅም በመፍጠር ሀገር አቀፍ የወሳኝኩነት ምዝገባ ስርዓቱን አንድ እርምጃ ወደፊት እንደሚወስድ ይጠበቃል፡፡