የፀረ-ሙስናና የብሔር ብሔረሰቦች ቀን የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት አመራሮችና ሰራተኞች አከበሩ

የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት አመራሮችና ሰራተኞች የፀረ-ሙስናና የብሔር ብሔረሰቦች ቀንን ህዳር 29/2014ዓ.ም በተቋሙ የስብሰባ አዳራሽ አከበሩ።

በተዘጋጀው መድረክ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የተቋሙ ም/ዋና ዳይሬክተር ወ/ሪት አበራሽ ታሪኩ የሥነምግባርና የፀረ-ሙስና ችግሮችን ለመፍታት የተቋማችን አመራርና መላው ሰራተኛ ጉዳዩን  በባለቤትነት መንፈስ እንዲሳተፉበት በማድረግና ግንዛቤ በመፍጠር፤ በፀረ-ሙስና ትግሉ ተቋማዊ ንቅናቄ እንዲፈጠር ጠንክረን በጋራ መስራት አለብን ሲሉ ገልፀዋል።

በተጨማሪም የተቋሙ ሰራተኞች ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለመግታት የስነምግባር ግንባታንና ሙስናን የመከላከል ስራን በጠንካራ ዲሲፕሊን በመምራት የተቋሙ ሀገራዊ የስታቲስቲክስ መረጃ ሰብስቦ ለተጠቃሚዎች የማሰራጨት ተልዕኮን ለማሳካት ሌብነትና ብልሹ አሰራርን ለማስቆም በቅንጅት መስራት ይጠበቅብናል ሲሉ ገልፀዋል።

የዘንድሮ ዓመት የፀረ-ሙስና ቀን  በዓለም አቀፍ ደረጃ ለአስራ ስምንተኛ ጊዜ በሀገራችን ደግሞ ለአስራ ሰባተኛ ጊዜ «በሥነምግባር የታነፀ አመራር ከሙስና ለፀዳች ኢትዮጵያ» በሚል መሪ ቃል ተከብሯል።  የሥነምግባር ችግሮችና ሙስና የሚያስከትላቸው ጉዳቶች ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር የተዘጋጀ ጽሁፍ በሥነምግባርና ፀረ-ሙስና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በአቶ ዳምጠው አበራ ቀርቦ በሰራተኞች ውይይት ተደርጎበታል። በዕለቱም ፀረ-ሙስናን ላይ ያተኮረ የጥያቄና መልስ ውድድር በማካሄድ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ ተሰርቷል።

በተጨማሪም የብሔር ብሔረሰቦችን ቀን «ወንድማማችነት ለሕብረብሔራዊ አንድነት» በሚል መሪ ቃል ለአስራ ስድስተኛ ጊዜ በተቋሙ የተከበረ ሲሆን ቀኑን ስናከብር አሸባሪው ቡድን በኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች መካከል የተከለውን የጥላቻ ግንብ በመናድ የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካ መብቶች እኩልነት የተረጋገጠበት፤ በኢትዮጵያዊ አንድነት ላይ ቆማ የበለፀገች ሀገር ለመገንባት ዳግም ቃል የሚገባበት መሆን እንደሚገባ ተገልጿል። በዕለቱም የተቋሙ ሰራተኞች ‘#NO MORE’ ወይም ‘‘በቃ’’ በማለት የምዕራቡ ዓለም አገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ያልተገባ ጫና እና ጣልቃ ገብነት በማውገዝ ድምፃቸውን አሰምተዋል።