የፕላን፣በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በተቋሙ የስራ ጉብኝት አደረጉ

ጥር 19/2015ዓ.ም በተከበሩ አቶ ደሳለኝ ወዳጆ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተመሩ የኮሚቴው አባላት በኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ዋና መ/ቤት የአንድ ቀን የስራ ጉብኝት አደረጉ።

የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር በከር ሻሌ ለቋሚ ኮሚቴ አባላት በጽ/ቤታቸው አቀባበል ያደረጉላቸው ሲሆን በቆይታቸው የስድስት ወር ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ገለፃ መስማት፣ ከሰራተኞች ጋር ውይይት ማድረግና በተለያዩ የስራ ክፍሎች በአካል ጉብኝት የማድረግ ተግባራትን አከናውነዋል።

በተደረገላቸው ሪፖርት ገለፃ ከሰራተኞች ጋር ባደረጉት ውይይትና በየስራ ክፍሎች ባደረጉት ጉብኝት ተቋሙ ሰፊና ውስብስብ ሙያዊ ሂደት የተከተለ የመረጃ መሰብሰብ፣ መተንተንና ማሰራጨት ተግባራትን እንደሚያከናውንና ለሀገራችን ሁለንተናዊ ልማት አስፈላጊ የሆነውን መረጃ የማቅረብ ተልዕኮ በተደራጀ መልኩ እያቀረበ የሚገኝ ተቋም እንደሆነ እንድንረዳ ያስቻለን ጠቃሚ ጉብኝት ነው ሲሉ ገልፀዋል።

ተቋሙ የመረጃ መሰብሰብ እስከ ሪፖርት ስርጭት ያሉትን ተግባራት ከወረቀት ነፃ በሆነ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም እያከናወነ ያለው ስራ በአወንታዊነት የሚወሰድና ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሁን የተጀመሩ ተቋማዊ ሪፎርም ተግባራትም ጥሩ መሆናቸውንና በአጭር ጊዜ መጠናቀቅ እንዳለባቸው እንዲሁም ከሰራተኞች የሚነሱ የመልካም አስተዳደር፣ የጥቅማ ጥቅምና ምቹ የስራ ቦታ አለመኖር፣ የንብረት አያያዝና አወጋገድና ከበጀት አጠቃቀም ጋር ተያይዘው የታዩትን ክፍተቶች በቀጣይ ጊዜያት ትኩረት መሻሻልና መፈታት እንዳለባቸውና ቋሚ ኮሚቴው ተቋሙ ለሚያከናውናቸው ተግባራት የሚያስፈልገውን እገዛ እንደሚያደርጉ ግብረ መልስ የሰጡ ሲሆን በመጨረሻም የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ከኮሚቴው አባላት በጥያቄ መልክ ለተነሱት ሀሳቦችና ግብረ መልስ ላይ ምላሽና አስተያየት በመስጠት ቋሚ ኮሚቴው በአካል በተቋሙ ተገኝቶ ላደረገው ጉብኝትና ለሰጠን ገንቢ ግብረ መልስ ያላቸው ምስጋና በማቅረብ ተቋሙ የጀመረውን የሪፎርም ስራዎች ለማሳካት የሚደረገውን ጥረት የቋሚ ኮሚቴው እገዛ እንደሚያስፈልጋቸው በመጠየቅ ጉብኝቱ ተጠናቋል።