የ2014ዓ.ም የግብርና ናሙና ጥናት ለማካሄድ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት እየተከናወነ ይገኛል፡፡

የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ የ2014 ዓመታዊ የግብርና ናሙና ጥናትን ለማካሄድ ከ19 /11/2013 እስከ 29/11/2013 ዓ.ም ድረስ በአዳማ ፓናፍሪክ ሆቴል ለ214 ስታቲሽያኖች፣ 12 ፕሮግራመሮችና ለቅፅ/ቤት ሀላፊዎች የአሰልጣኞች ስልጠና ሰጠ፡፡

ስልጠናውን በንግግር የከፈቱት የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢራቱ ይገዙ እንደገለፁት የግብርና ናሙና ጥናት ለማካሄድ ሰፊ ዝግጅት ሲካሄድ መቆየቱን አስታውሰው በዘንድሮ የግብርና ናሙና ጥናት በአማርኛ ብቻ ይዘጋጅ የነበረው መጠየቅ በኦሮምኛ ቋንቋ ተተርጉሞ በአማረኛና በኦሮምኛ ቋንቋ መጠይቅ መዘጋጀቱን  ገልፀው በቀጣይም በተለያዩ በሀገራችን ቋንቋዎች መጠይቆችን በማዘጋጀት የተሻለ ጥራት ያለው መረጃ ለማግኘት የሚሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ አክለው እንደገለፁት ሰልጣኞች ከስልጠናው ተገቢውን ግንዛቤ በመውሰድ በቀጣይ ለመረጃ ሰብሳቢዎች በሚሰጠው ስልጠና በተገቢው መልኩ በመዘጋጀት ሀላፊነታቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው የስራ መመሪያ ሰተዋል፡፡

በዚህ አመት ከሌላ ጊዜ በተለየ መልኩ ከተከናወኑ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት መካከል ከመረጃ ተጠቃሚዎች ፣ ከግብርና ሚኒስቴርና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ፍላጎት መሰረት በማድረግ መጠየቁና ማኗሉን ክለሳ በማድረግ እንዲሁም በቀጣይ አስር አመታት የዘርፍ የልማት ዕቅድ የመረጃ ፍላጎት ከግምት ውስጥ በማስገባት ዝግጅት መደረጉን አቶ አህመድ ኢብራሂም የግብርና የተፈጥሮ ሀብትና ከባባቢ ዳይሬክተር አስረድተዋል፡፡

ከጥናቱ የሚሰበሰቡ ዋና ዋና የመረጃ ዓይነቶችም የዋና መኸር ወቅት (ማሳ ስፋት፣ የምርታማነት ዕድገት፣ የእርሻ አስተዳደር፣ መሬት አጠቃቀም)፣ አጠቃላይ የቤት እንስሳት ሁኔታ (በብዛት፣ በአይነት፣ በዕድሜ፣ በፆታ፣ በአገልግሎትና በተዋፅኦ)፣ የደረቅ ወቅት መስኖ እርሻ፣ የበልግ ወቅት እርሻ፣ የሰፋፊና መካከለኛ የንግድ እርሻ ፣ የዓሳ ሀብት ፣ የሰብልና እንስሳት ተዋፅኦ አጠቃቀም)፣ ቅድመ እና ድህረ ሰብል ምርት ብክነት፣ የዓሳ ሀብትና ቅድመ እና ድህረ ሰብል ምርት ብክነት ሲሆኑ ሁሉም ጥናቶች እንደየወቅታቸው በወጣላቸው መርሃ ግብር ቅደም ተከተል ይካሄዳሉ፡፡

ከጥናቱ የሚገኙ መረጃዎችም መንግስት ምርትና ምርታማነትን ወደተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገር ለሚያወጣቸው ዕቅዶችና ፖሊሲዎች እንደ ግብአትነት የሚያገለግሉ ሲሆኑ በዘርፉ የተሰማሩ ኢንቬስተሮች፣  ተመራማሪዎችምና ለመረጃ ተጠቃሚዎች ያገለግላል፡፡

በቀጣይ በየቅ/ፅ/ቤቶች ለመረጃ ሰብሳቢዎች ከነሐሴ 10 እስከ 29/2013 ዓ.ም እንዲሁም ከነሐሴ 30 ጀምሮ ከመስክ መረጃ የመሰብሰብ ተግባራት እንደሚጀመር ከወጣው መርሀግብር ለመረዳት ተችሏል፡፡