በሁለተኛው የብሄራዊ ስታቲቲክስ ልማት ስትራቴጂ አፈጻጸምና በቀጣይ አምስት አመት የስትራቴጂ ዕቅድ ዝግጅት ላይ ውይይት ተካሄደ

በሁለተኛው የብሄራዊ ስታቲቲክስ ልማት ስትራቴጂ አፈጻጸምና በቀጣይ አምስት አመት የስትራቴጂ ዕቅድ ዝግጅት ላይ ውይይት ተካሄደ

የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ በሁለተኛው የብሄራዊ ስታቲቲክስ ልማት ስትራቴጂ (NSDSII) አፈጻጸምና በቀጣይ አምስት አመት የስትራቴጂ ዕቅድ (NSDSIII) ዝግጅት ላይ ከታህሳስ 21-23/2013ዓ.ም ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ በኢሊሌ ሆቴል አዘጋጀ፡፡

የምክክር መድረኩን በንግግር የከፈቱት የኤጀንሲው ዋና ዳ/ር አቶ ቢራቱ ይገዙ ተቋሙ ሁለተኛውን የአምስት አመት ብሄራዊ የስታቲስቲክስ ልማት ስትራቴጂ ዕቅድ አዘጋጅቶ ላለፉት አምስት አመታት ሲተገብር እንደቆየና የዕቅዱ ጊዜ በመጠናቀቅ ላይ በመሆኑ ያለፉትን አምስት አመታት አፈጻጸም መገምገምና ቀጣይ የአምስት አመት ዕቅድ ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም ዋናዳ/ሩ ያለፉት አምስት ዓመታት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት እንደሚደረግበትና ለቀጣይ አምስት ዓመታት የሚኖሩትን የመረጃ ፍላጎቶች ከሴክተር መ/ቤቶችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት የመሰብሰብ ስራ እንደሚሰራ አብራርተው ለቀጣይ አምስት አመታት የስታቲስቲክስ ዕቅድ ዝግጅት ያለፈው አምስት አመት የስራ ዕቅድ አፈጻጸምና የአገሪቱን የቀጣይ አስር አመት ዕቅድ መመዘኛ ስርዓት እንደዋና ግብአትነት እንደሚወሰድና በተጨማሪም አገሪቱ ለመተግበር ቃል የገባችው የአለም አቀፍና አህጉር አቀፍ የዘላቂ ልማት ግቦች፣ የአፍሪካ አጀንዳ 2063፣ የኢጋድ ዕቅድና ሌሎች ፍላጎቶችን ከግምት ውስጥ እንደሚያስገባ ገልጸዋል፡፡  

በእለቱ በሁለተኛው የብሄራዊ ስታቲቲክስ ልማት ስትራቴጂ አፈጻጸም ላይ ሪፖርት የቀረበ ሲሆን ባለፉት አምስት አመታት በመረጃ ዕድገት፣ ጥራት፣ አቅርቦት፣ ትንተና፣ ስርጭትና አጠቃቀም፤ የመረጃ ሽፋንን መጨመር፣ ሜትዳሎጂን ማሻሻል፣ ስርአተ ጾታን በስታቲስቲክስ ማካተትና የተቋሙን መሰረተ ልማት ማሻሻል ስትራቴጂክ ዕቅዶች ላይ የተሸለ አፈጻጸም እንደተመዘገበ ና የስታቲስቲክስ ህጉን ማሻሻል፣ የብሄራዊ ስታቲስቲክስ ስርዓት ማስተባበርና ማጠናቀርና የስታቲስቲክስ ኮሚውኒኬሽንና ጉዳዮች ዕቅድ አፈጻጸም ላይ እጥረቶች እንደታዩ ለነዚህም ውስንነቶች የህዝብና ቤት ቆጠራ መራዘም፣ የስታቲስቲክስ ስርዓት ህጉ ላይ የሚታ ክፍተቶች፣ በጀት በታሰበው ጊዜ አለመገኘቱ፣ የኮቪድ-19 ወረርሺኝ፣ በተለያዩ ቦታዎች የተከሰቱ የፀጥታ አለመረጋጋትና መሰል ችግሮች እንደሆኑ ከሪፖርቱ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በውይይት መድረኩ የማዕከላዊ ስታቲስቲስቲክስ ኤጀንሲ አመራሮችና ከፍተኛ ባለሞያዎች፣ ሴክተር መ/ቤቶች፣ ዩኒቨርስቶዎች፣ የምርምር ተቋማት፣ የሙያ ማህበራትና ከሌሎች ባለድርሻ አካልት የተወጣጡ 75 ተሳታፊዎች የተገኙበት ሲሆን መድረኩ በአለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍና በተባበሩት መንግስታት የስታቲስቲክስ ክፍልና በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የቴክኒክ ድጋፍ የተዘጋጀ ነው፡፡