የስርዓተ ፆታ ስታቲስቲክስ አመላካቾች ላይ የተዘጋጀ መፅሀፍ ይፋ ሆነ

የስርዓተ ፆታ ስታቲስቲክስ አመላካቾች ላይ የተዘጋጀ መፅሀፍ ይፋ ሆነ

የስርዓተ ፆታ ስታቲሰስቲክስ አመላካቾች ላይ ትኩረቱን ያደረገ የእጅ መፅሀፍ /Handbook/ ታህሳስ 15-16/2013 ዓ.ም ለመረጃ ተጠቃሚዎች ይፋ ተደረገ። ይህ የስርዓተ ፆታ ስታቲስቲክስ አመላካቾች መፅሀፍ አዳዲስ የስርዓተ ፆታ አመላካቾችን በመጨመር የተዘጋጀ ሲሆን በስርዓተ ፆታ ስታቲስቲክስ ላይ ያሉ የመረጃ ክፍተቶችን ለማገዝ እንደሚረዳ ተገልጿል። ይህ መፅሀፍ በሁለት ከፍተኛ የስታቲስቲክስ ባለሙያዎች ወ/ሮ አስናቀች ሀብታሙና በአቶ አሸናፊ ስዩም የተዘጋጀ ሲሆን በተጨማሪም በUNFPA እና በUN-WOMEN የገንዘብና ቴክኒካል ድጋፍ እንደተዘጋጀ ገልፀዋል።

የዚህ መፅሀፍ ዓላማ በማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ለተመረጡት በጣም አስፈላጊ በሆኑ የስርዓተ-ፆታ ስታቲስቲክስ አመላካቾች ማብራሪያና መግለጫ ለመስጠትና ከስርዓተ-ፆታ ጋር የተያያዙ መረጃዎችን ለመገምገምና በብሔራዊ ሰታቲስቲክስ የመረጃ አቀማመጥ ውስጥ የሌሉ መረጃዎች ለመለየት እንደሆነ በመፅሀፉ ተገልጿል። በስርዓተ-ፆታ ስታቲስቲክስ የተመሰረቱ አመላካቾችን ስሌት በተመለከተ የመረጃዎችንና የአመላካቾችን ጥንካሬና ውስንነት ለተጠቃሚዎች በማሳየት መረጃ ተጠቃሚዎች ትክክለኛ ስሌት እንዲያገኙ ያደርጋል። በተጨማሪም ይህ መፅሀፍ የስርዓተ-ፆታ ስታቲስቲክስ መረጃን ጠለቅ ባለ ሁኔታ በማየት ብዙ የስርዓተ-ፆታ ስታቲስቲክስ መረጃዎችን ማውጣት እንደሚቻል ተገልጿል።

በመፅሀፉ ማጠቃለያ ላይ እንደተገለፀው በቀጣይ በስነ-ሕዝብ፣ በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚና በግብርና ዘርፍ የስርዓተ-ፆታ መረጃ በማካተት፣ በፍልሰት ስታቲስቲክስና በስራ ፍልሰት ላይ ከፍተኛ የሆነ የስርዓተ ፆታ መረጃ ክፍተት ስላለ መረጃው እንዲገኝ በማድረግ ረገድ ያለውን የመረጃ ክፍተት ለመሙላት በቀጣይ እንደሚሰራ ተገልጿል።