የመረጃ ተጠቃሚዎች ተሳትፎ ስትራቴጂ ረቂቅ ሰነድ ላይ ውይይት ተደረገ

በማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ የተዘጋጀው የመረጃ ተጠቃሚዎች ተሳትፎ ስትራቴጂ ረቂቅ ሰነድ (user engagement strategy draft document) ላይ ጥቅምት 27/2012 ዓ.ም በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ውይይት ተካሄደ።

ከፌዴራል መንግስት የተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች የተውጣጡ የመረጃ ተጠቃሚዎች በተሳተፉበት የውይይት መድረክ ላይ በመገኘት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢራቱ ይገዙ የተቋማችን ተልዕኮ የተለያዩ መረጃዎችን በመሰብሰብ፣ በማጠናቀር፣ ለተጠቃሚዎች ማሰራጨትና ብሔራዊ ስታቲስቲክስ ስርዓቱን ማስተባበር መሆኑን ገልፀው በአሁኑ ወቅት በሀገር ደረጃ ያለውን የመረጃ ፍላጎት ለማሟላት ተቋሙ ሁሉን አቀፍ የሪፎርም (reform) ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሆነ፤ ከዚህ ተግባር አንዱ በምንሰራቸው ስራዎች ላይ የመረጃ ተጠቃሚዎች ተሳትፎ ማሳደግ የሚያስችል የመረጃ ተጠቃሚዎች እርካታ (user satisfaction survey) ጥናት በማካሄድ እንደተቋም ከተጠቃሚዎች አቅጣጫ ያለውን ፍላጎት መለየት እንደተቻለ ከዚሁም በመነሳት የመረጃ ተጠቃሚዎች ስትራቴጂ መነሻ ሰነድ ለማዘጋጀት ተችሏል። በዛሬው ውይይትም ከተሳታፊዎቹ ሰነዱን ለማጠናከር የሚረዱ ሀሳቦች እንደሚጠበቅ አብራርተዋል።

የሀገሪቱ የመረጃ ተጠቃሚዎች ተሳትፎ ስትራቴጂ ራዕይ በ2024 ውጤታማና ጥራቱን የጠበቀ መረጃ በማመንጨት ለተጠቃሚዎች ማቅረብ መሆኑ ከሰነዱ መረዳት ተችሏል።

በመነሻ ሰነዱ የተካተቱ መረጃ ተጠቃሚዎች ፍላጎት፣ የግንዛቤ እጥረት፣ በመረጃ ማመንጨት ላይ እንዴት መሳተፍ እንደሚችሉ እንዲሁም የአመንጪና ተጠቃሚዎች ኃላፊነትና የሥራ ክፍፍል ላይ የተዘጋጁ ገለፃዎች በብሔራዊ ስታቲስቲክስ ጥራትና ደረጃ ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ ባለሙያዎች ቀርበው በተሳታፊዎች ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል።

በውይይቱም ከተሳታፊዎች ለተነሱት ጥያቄዎች እና ተጨማሪ ሀሳቦች ላይ በብሔራዊ ስታቲስቲክስ ማስተባበሪያ እና ኦፕሬሽን ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር ወ/ት አበራሽ ታሪኩ ምላሽና ቀጣይ አቅጣጫ የተሰጠበት ሲሆን ሰነዱ በውይይቱ ከተሳታፊዎች የተሰጡትን አስተያየቶች በማካተት በቅርብ ጊዜ ውስጥ ወደ ተግባር እንደሚገባ አስረድተዋል።   

ከፌዴራል የብሔራዊ ስታቲስቲክስ ሥርዓት አባል (NSS) ተቋማት የተውጣጡ ከ50 በላይ የሚሆኑ ባለሙያዎች በውይይቱ ተሳታፊ ነበሩ።