የአስተዳደር፣ የሰላምና ደህንነት ነክ ጉዳዮች በሚመለከት ጥናት ለማካሄድ ዝግጅት እተደረገ መሆኑን ተገለፀ

በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የአስተዳደር፣ የሰላምና ደህንነት ስታቲስቲካዊ ጥናት /Governace, peace and security statistics survey/ ለማካሄድ በመጠይቆች ይዘትና ሜቴዶሎጂ ዙርያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በፍሬንድሺፕ ኢንተርናሽናል ሆቴል በ18/06/2014 ዓ.ም የአንድ ቀን ውይይት ተካሄደ፡፡

ውይይቱን በንግግር የከፈቱት የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ አሳልፈው አበራ የህግ፣ የአስተዳደርና የአሰራር ለውጦች ለማምጣት መንግስት በተቋማት ላይ እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀው፤በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቋማት በተለያዩ ዘርፎች መረጃዎች እንዲያጠናቅሩ ከሚነሱት ጥያቄዎች መካከል በማህበራዊ ዘርፍ በተለይም በመንግስት ሰላምና ፀጥታ ዙርያ አንዱ ሲሆን በሀገራችን በዘርፉ የተደራጀ መረጃ በየተቋማቱ በሚፈለገው ደረጃ አለለማለት አያስደፍርም በመሆኑ ለመጀመሪያ ጊዜ መረጃው እንዲሰበሰብ በብሄራዊ ስትራቴጂክ ዕቅድ ውስጥ ተካቶ ከዚህ አንፃር የሚታየውን የመረጃ ክፍተት ለመሙላት ተቋማችን እንቅስቃሴ ላይ ይገኛል ሲሉ በመክፈቻ ንግግራቸው ገልፀዋል፡፡

በአፍሪካ ህብረትና በተባበሩት መንግስታት ሀገራት ጥናቱን በማካሄድ መረጃዎችን ማደራጀት እንዳለባቸው አቅጣጫ የተቀመጠ ሲሆን መረጃው የመንግስታዊ ተቋማት አገልግሎት አሳጣጥ፣ የዜጎች ደህንነትና ሰብአዊ መብቶች አያያዝ እንዲሻሻሉ መረጃዎቹ ግብዓት ስለሚሆኑ ከፍተኛ አስተዋፆ እንደሚያበረክት መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ በመሆኑም በሀገራችን በዚህ ዘርፍ የሚታየውን ክፍተት ለመሙላት የአለም አቀፍ ሀገራት ሰነዶችን በማየትና ልምድ በመውሰድ ሜቴዶሎጂና መጠይቅ የማዘጋጀት ስራ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የጥናቱ ዋና ዓላማ ህብረተሰቡ የመንግስት የዜጎች መብት አያያዝ፣ የአስፈፃሚ አካላት፣ የሙስና፣ምርጫና የምርጫ ስርዓት፣ የዜጎች ደህንነት በአጠቃላይ የመንግስት ስርዓቱ ላይ የህብረተሰቡ አስተያየት ምን ይመስላል የሚለውን መረጃ በመሰብሰብ የዜጎች ድምፅ ለመሆን ያለመ ጥናት ሲሆን መንግስት መረጃውን እንደግብኣት በመውሰድ የዜጎችን ጥያቄና ፍላጎት ለማሟላት እንዲሰራ የሚያግዝ መረጃዎች ከጥናቱ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

በጥናቱ የመንግስታዊ ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ፣ፍትህ ሂደት፣ ምርጫና የምርጫ ስርዓት፣ ዲሞክራሳዊ አስተዳደር፣ ግልፅነትና ተጠያቂነት፣ ሰላምና ደህንነት እንዲሁም ግጭት ላይ ያተኮሩ መረጃዎችን እንደሚሰበሰቡ ከቀረበው ገለፃ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በዚህ የባለድርሻ ውይይት መድረክ ላይ ከጥናቱ የሚገኘው መረጃ በቀጥታ ተጠቃሚ የሆኑና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው የተለያዩ የፌደራል መንግስት መስሪያ ቤቶች የተገኙበት ሲሆን በተቋሙ በቀረቡት የጥናቱ ሜቴዶሎጂና ለመጠየቅ በተዘጋጁ ጥያቁዎች ላይ ያላቸውን ሀሳብና ተጨማሪ እንዲካተት የሚፈልጉት ጥያቄዎች አንስተዋል፡፡

በመጨረሻም ከባለድርሻ አካላት የተነሱትን ገንቢና ጠቃሚ ሀሳቦችን በማካተት ወደ ሙከራ ጥናትና በዋናው የመስክ መረጃ የመሰብሰብ ተግባር እንደሚካሄድ ከስነህዝብ ስታቲስቲክስ የስራ ሂደት የስራ መርሃ-ግብር ለመረዳት ተችሏል፡፡