ተከታታይ የከተማ የስራ ስምሪት ጥናትን ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ ነው

የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ተከታታይ የከተማ የስራ ስምሪት ናሙና ጥናትን ለማካሄድ ከጥር 05-21/2014 ዓ.ም በአዳማ ለ203፣ ሀዋሳ ለ157፣ ጅማ ለ164ና ድሬዳዋ ለ167 በአጠቃላይ ለ691 መረጃ ሰብሳቢዎች፣ ተቆጣጣሪዎችና ስታቲሽያኖች ስልጠና በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡

ስልጠናውን በንግግር የከፈቱት የተቋሙ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አማረ ለገሰ ተከታታይ የከተማ የስራ ስምሪት ጥናት እጅግ አስፈላጊና መንግስት የሚጠብቀው ጥናት እንደሆነ ገልጸው ባለፉት አመታት በአመት አንድ ጊዜ የሚጠና የነበረ ሲሆን አሁን ግን ከጠቀሜታው አኳያ በአመት ሁለት ጊዜ እንዲጠና ከመንግስት መወሰኑን ተናግረዋል፡፡

ጥናቱ በኢትዮጵያ ከተሞች ያለውን የሰው ሃይል ብዛት፣ በስራ ላይ የተሰማራውን፣ ለስራ የደረሰውን፣ በእድሜ ፣በጉዳትና በተለያዩ ምክንያቶች በስራ ላይ መሰማራት የማይችሉ የከተሞች የስራ አጥነት ምጣኔ መረጃዎችን የሚያስገኝ ሲሆን በተጨማሪም በዲግሪ፣ በዲፕሎም፣ በኢኮኖሚ፣ በግብርና፣ በኢንደስትሪ፣ በመንግስት መ/ቤቶችና መደበኛ ባልሆነ የስራ ዘርፍ የተሰማራውን የሰው ሃይል መረጃን ለማግኘትና ደሞዝና ምንዳን ለማስላት እንደሚጠቅም ያስረዱት ም/ዋ/ዳሩ በመስክ መረጃ የመሰብሰብ ስራ ላይ የሚሰማሩ ባለሞያዎች በሙሉ ታማኝነትና ሀገራዊ ስሜት ጥናቱ ለታለመለት አላማ እንዲውል በትጋት እንዲሰሩ አሳስበዋል፡፡

በጥናቱ የመስክ መረጃ መሰብሰብ ሥራ ሙሉ በሙሉ በታብሌት ቴክኖሎጂ የሚከናወን ሲሆን ይህም የመረጃውን ጥራት ወቅታዊነትና ተዓማኒነት ለማሳደግ ያለውን ፋይዳ ተረድታችሁ በስልጠናው ጊዜ የቴክኖሎጂ አጠቃቀሙ ላይ የሚሰጡትን ስልጠናዎች በሚገባ መከታተል እንዳለባቸው ለሰልጣኞች አሰረድተዋል፡፡

ጥናቱ በርከት ያሉ አላማዎች ያሉት ሲሆን ከነዚህም መካከል ሀገሪቷ በከተማ ደረጃ ያላትን ለስራ የደረሰና ዝግጁ የሆነ የሰው ሀይል/ Active population/ እና በተለያዩ ምክንያት በስራ ላይ ሊሰማራ ያልቻለውን / not active population/ የሰው ሀይል ብዛት ስታቲስቲካዊ መረጃ ለማስገኘት፣ በጥናቱ ወቅት በስራ ላይ የተሰማራውን/ Employed population/ ብዛትና ስራ የሌላቸውን ሰዎች / Unemployed population/ መጠን ለማግኘት፣ ሀገሪቱ በከተማ ደረጃ ያላትን በስራ ተሰማራና ያልተሰማራ ሰው ሀይል በስልጠና/በሙያ ሁኔታ ለመለየት፣በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በአገልግሎት ሰጪና በመንግስት መ/ቤቶች ወ.ዘ.ተ የሰው ሀይል ተሳትፎን ለመገምገም፣ በመደበኛና መደበኛ ባልሆነ የስራ ዘርፍ የሚሳተፈውን የሰው ሀይል መጠን መረጃ ማስገኘት አበይት ዓላማዎች ናቸው፡፡

ይህ ጥናት የሚካሄደው በመላ ሀገሪቱ በሳይንሳዊ ዘዴ በናሙና በተመረጡ በአጠቃላይ 1,110 የቆጠራ ቦታዎች ሲሆን 28,860 ቤተሰቦችን ይሸፍናል፡፡

ለጥናቱ በመስክ ከጥር 25- የካቲት 03/2014ዓ.ም መረጃዎች የሚሰበሰቡ ሲሆን ሚያዝያ 30/2014ዓ.ም ለተጠቃሚዎች ይፋ እንደሚደረግ ይጠበቃል፡፡ የጥናቱን ውጤት በዋናነት መንግስት ለሚያካሂዳቸው አዳዲስ ፖሊሲዎችና የረዥምና ለአጭር ጊዜ ዕቅዶች፣እንዲሁም ለስራ አጥ የስራ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት፣ የሚጠቀምበት ሲሆን ለፖሊሲ ቀረጻ፣ ለዕቅድ አውጭዎች፣ ተመራማሪዎች፣ ለኢንቨስተሮች እንዲሁም ለሌሎች ዓለም አቀፋና የአገር መረጃ ተጠቃሚዎች በዘርፉ የሚፈለጉ መረጃዎችን ለማስገኘት፣ በሃገሪቱ ያለውን የሥራና የሥራ አጥ ሁኔታ አመላካች መረጃዎችን ለማግኘት እንደመነሻ ግብአትነት ያገለግላለል፡፡