የመረጃ ተጠቃሚዎች ተሳትፎ ስትራቴጂ ትግበራ ላይ ውይይት ተካሄደ

የመረጃ ተጠቃሚዎች ተሳትፎ ስትራቴጂ ሰነድ ትግበራ ላይ በብሔራዊ ስታቲስቲክስ ሲስተም ውስጥ ካሉ ሴክተር መስሪያ ቤቶች፣ከማዕከላዊ ስታቲስክስ ኤጀንሲ የተውጣጡ የስራ ሀላፊዎችና ከፍተኛ ባለሙያዎች በተገኙበት ከመጋቢት 2 – 4/2012 ዓ.ም በቢሾፍቱ ከተማ ውይይት ተካሄደ።

በኤጀንሲው የስታቲስቲክስ ጥናቶችና ቆጠራዎች ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አማረ ለገሰ መድረኩን በንግግር ሲከፍቱ ማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ እንደሀገሪቷ ቀዳሚ የመረጃ ምንጭነቱ ጥራቱን የጠበቀ መረጃን በመሰብሰብ፣ በማጠናቀር ለተጠቃሚዎች እንደሚያሰራጭ አስታውሰው ሰነዱ በብሔራዊ ስታቲስቲክስ ሲስተም ውስጥ ካሉ ተቋማት በጋራ በመስራት ለተጠቃሚዎችና ስርዓት ውስጥ ላሉ ተቋማት ጥራቱን የጠበቀ መረጃ ውጤታማ በሆነ መልኩ ለማቅረብ እንደሚያስችል አያይዘው ገልፀዋል።

ከዚህ በፊት በተደረጉት ሁለት የውይይት መድረኮች የመረጃ ተጠቃሚዎችን ፍላጎት ባካተተ መልኩ የተዘጋጀው የመረጃ ተጠቃሚዎች ተሳትፎ (User Engagement strategy) ስትራቴጂ ወደ ትግበራ ለማስግባት የሚሰሩ እንደሙያቸው ከሁሉም ባለድርሻ አካላት የተውጣጡ ሶስት ቴክኒካል ኮሚቴ መቋቋሙን ያስረዱት የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ የብሔራዊ ስታቲስቲክስ ማስተባበሪያና ኦፕሬሽን ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር ወ/ት አበራሽ ታሪኩ በቀጣይ ይህ ቴክኒካል ኮሚቴ በየሶስት ወር እየተገናኘ የስትራቴጂው ትግበራ ሂደትና ውጤቱ ላይ ውይይት እንደሚያደርግ በመጥቀስ፣ በዕለቱም የስትራቴጂ ትግበራውን በሚመለከት የቀረበውን ገለፃ መነሻ በማድረግ በተሰጣቸው የስራ ክፍፍል ወደ ተግባር ለመቀየር የሚያስችል ውይይት በየቡድናቸው በማድረግ የቀጣይ ድርጊት መርሀ ግብር አዘጋጅተው ለመድረኩ በማቅረብ አስተያየቶች እንዲሰጥበት ተደርጓል።

በመጨረሻም ም/ዋና ዳይሬክተሯ ማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ከተሰጠው ተልዕኮ አንዱ ብሔራዊ ስታቲስቲክስ ስርዓቱን ማስተባበር፣ በማብቃት በሂደቱም ወጥነት ያለውና የተገናዘበ ሀገራዊ ስታቲስቲክስ መረጃዎችን አቅርቦት ስርዓት መፍጠር ሲሆን የዚህ ዓይነቱ የመረጃ ተጠቃሚዎች ተሳትፎ ስትራቴጂ ወደምንፈልገው ለመድረስ ያለው ሚና የጎላ በመሆኑ ኤጀንሲያችን ይህ ስትራቴጂ በተሟላ መልኩ ተግባራዊ እንዲሆን ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር እንደሚሰራ ተገልጿል።

በውይይት መድረኩ ከፌዴራል ሴክተር መስሪያ ቤቶች፣ ከብሔራዊ ባንክ፣ ከሚዲያ ተቋማት፣ ከምርምር ተቋማትና ከማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ የተውጣጡ ከ60 በላይ ከፍተኛ ባለሙያዎችና የስራ ሀላፊዎች ተሳትፈዋል።