የስታቲስቲክ ለውጤት ውጤታማ መሆኑ ተገለፀ
የስታቲስቲክ ለውጤት ውጤታማ መሆኑ ተገለፀ

የስታቲስቲክስ ለውጤት ፕሮጀክት ውጤታማ ሥራዎች ማከናወኑ ተጠቆመ

በዓለም ባንክ የፋይናንስ ድጋፍ ባለፉት አምስት ዓመታት  የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲን የመረጃ መሰብሰብ፣ ማጠናቀር እና ሥርጭት ሂደት ለማሻሻል ታሳቢ ተደርጎ ሲተገብር የቆየው የስታቲስቲክስ ለውጤት ፕሮጀክት አፈጻጸም ስኬታማ መሆኑ ተገለጸ።

ከመስከረም 12 እስከ 13/2012 ዓ.ም በኤጀንሲው አዲስ የስብሰባ አዳራሽ በተካሄደው አገር አቀፍ የስታቲስቲክስ መረጃ ሥርጭት እና የስታቲስቲክስ ለውጤት ፕሮጀክት መዝጊያ ወርክሾፕ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር እዮብ ተካልኝ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግሥት ስታቲስቲክስ መረጃዎች ለፖሊሲ ቀረፃ፣ ለልማት ዕቅዶች ትግበራና አፈጻጸም ክትትል ያላቸውን ፋይዳ በመገንዘብና  የብሔራዊ ስታቲስቲክስ ሥርዓቱን ለማዘመንና ለማጠናከር እ.ኤ.አ ሰኔ 2014 የስታቲስቲክስ ለውጤት ፕሮጀክት በመቅረፅ የ15.5 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ከዓለም ባንክ ጋር በመፈራረም ወደ ትግበራ መግባቱን አስታውሰው ፕሮጀክቱ ባለፉት አምስት ዓመታት የተቋሙ የመሠረተ ልማት፣ የቴክኖሎጂ ግብአቶች በማሟላት እንዲሁም የሰው ኃይል የመፈፀም አቅም በማሻሻል ረገድ ያከናወናቸው ተግባራት ስኬታማ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በአሁኑ ጊዜ ሀገራችን በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር አቢይ አህመድ አመንጪነት አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ዕቅድ ማዘጋጀቷን የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታው ኤጀንሲው በፕሮጀክቱ ድጋፍ የተፈጠሩለትን አቅሞች በተገቢ መልኩ በመጠቀም ለዚህ ዕቅድ ትግበራ ክትትልና ግምገማ የሚያስፈልጉትን የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስታቲስቲክስ መረጃዎች በጥራትና በወቅቱ የማቅረብ ኃላፊነቱን በተገቢ መልኩ መወጣት እንደሚጠበቅበት ገልፀው መንግሥት ከሀገሪቱ ዕድገት ጋር የሚራመድ የስታቲስቲክስ ተቋም የመገንባት ተግባር በቀጣይ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

በዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ተወካይ ሚስ ናታሊያ ሚሌንኮ በበኩላቸው ባንኩ በማደግ ላይ ያሉ አገራትን የስታቲስቲክስ ተቋማት ለማጠናከር ፕሮጀክት ቀርፆ ሲሰራ መቆየቱን ጠቁመው ኢትዮጵያም ከነዚህ ሀገራት አንዷ በመሆን የዕገዛው ተጠቃሚ መሆኗን ገልጸው ባንኩ የሀገሪቱ ኦፊሻል ስታቲስቲክስ መረጃ ምንጭ የሆነው ማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ያለመውን በዓለም ታማኝና ጥራቱን የጠበቀ የስታቲስቲክስ አቅራቢ ተቋም የመሆን ራዕዩን ለማሳካት እና ወደ ዲጂታል ዳታ ቴክኖሎጂ የሚያደርገው ሽግግርን መደገፍን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢራቱ ይገዙ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ኤጀንሲው ያሉበትን የመሠረተ ልማት እጥረቶች ከመቅረፍ አንፃር ስድስት የቅ/ጽ/ቤት ህንፃ፣ በዋና መሥሪያ ቤት የስብሰባ አዳራሽ፣ መንግሥት ያስገነባቸው ሁለት ህንፃዎች ቢሮ ቁሳቁስ በማሟላት እንዲሁም ነባር የተቋሙ ህንፃዎች  ለሥልጠና ማዕከል ሆኖ ማገልገል በሚያስችል ደረጃ የእድሳት ተግባር በማከናወንና ለመረጃ መሰብሰብ የሚውሉ የቴክኖሎጂ ግብአቶችን በግዥ ከማሟላትም በተጨማሪ የሰው ኃይል አቅም ግንባታ ላይ ባለፉት አምስት ዓመታት ያከናወናቸው ተግባራት ተቋሙ በሀገሪቱ የልማት ዕቅዶችና ፖሊሲ ቀረፃ የሚፈለጉና እያደገ የመጣውን የመረጃ ፍላጎት ለማሟላት የሚደረገውን ጥረት ከማገዝ አኳያ ያለው ፋይዳ የጎላ መሆኑን አብራርተዋል።

በመጨረሻም ዋና ዳይሬክተሩ የፕሮጀክቱ አፈፃፀም ውጤታማ እንዲሆን ከፍተኛ ድጋፍ እና ዕገዛ ላደረጉት ለኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግሥት፣ ለዓለም ባንክና ለሌሎች ባለድርሻ አካላት ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በወርክሾፑ ላይ ከዓለም አቀፍ የልማት አጋር ድርጅቶች፣ ከብሔራዊ የስታቲስቲክስ አባል ተቋማት፣ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ከተለያዩ የሙያ ማህበራት የተውጣጡ እንዲሁም የሴኔጋል የጋና የስታቲስቲክስ ቢሮ ኃላፊዎች በአጠቃላይ ከ200 በላይ የሆኑ አካላት የተሳተፉ ሲሆን በፕሮጀክቱ ድጋፍ የተሰሩ የስብሰባ አዳራሽና ዕድሳት የተደረገላቸው የሥልጠና ማዕከላት ተመርቀዋል።