የሰው ሀይልና ፍልሰት ጥናት የመስክ ሥራ ተጠናቀቀ

ማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ከመላ ሀገሪቱ በናሙና በተመረጡት 1,876 የቆጠራ ቦታና 51,000 ቤተሰቦች ላይ ከጥር 17 እስከ የካቲት 11/2013 ዓ.ም ሲያካሄድ የቆየው የሰው ሀይልና ፍሰት ጥናት የመስክ ስራ ተጠናቀቀ፡፡

የሰው ሀይልና ፍልሰት ጥናት፤በሀገር አቀፍ፣በክልል፣በከተማና በገጠር ለስራ የደረሰና ዝግጁ የሆነ የሰው ሀይል/Active Population/፣ በተለያዩ ምክንያቶች በሥራ ላይ ሊሰማራ ያልቻለውን /Not Active Population/ እንዲሁም በጥናቱ ወቅት በሥራ ላይ የተሰማራውን/Employed Population/ እና ሥራ የሌላቸውን /Unemployed/ ሰው ሀይል ብዛት ና መሠረታዊ ባህሪያትና ስርጭታቸው የሚመለከቱ መረጃዎች ይገኙበታል፡፡

በሀገር አቀፍና ክልል ደረጃ  የፍልሰተኞች ብዛትና የሥነ ህዝብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ባህሪያትን እንዲሁም ከሀገር ውጭ ፈልሰው የሚገኙትና ኢትዮጲያውያን ብዛት ያሉበት ሀገር፣የቆዩበት ጊዜ፣የፈለሱበት ምክንያትና ሌሎች ባህሪያት የሚመለከቱ መረጃዎች ከጥናቱ እንደሚገኙ፤ በመጨማሪም ስለ ኮረና ቫይረስ ቤተሰቦችና አባላት ያላቸው ግንዛቤ፣ የመከላከል ተግባራት፣በወረርሽኙ ያጋጠሙ የኢኮኖሚያዊ ማህበራዊ ችግሮችን የሚያመለክቱ መረጃዎች በዚሁ ጥናት ተካቶ እንደሚሰበሰቡ ከጥናቱ  መርሃ ግብር ማወቅ ተችልዋል፡፡

ከጥናቱ የሚገኘውን መረጃ ጥራት ለማስጠበቅ መደረግ ያለባቸው የሰው ሀይል ስልጠና፣የሜቶዶሎጂ፣የቴክኖሎጂ እና የመስክ ስራ ክትትል ዝግጅት በተሟላ መልክ በማድረግ ወደ ስራ የተገባ ሲሆን መረጃ መሰብሰቡ ተግባር ሙሉ በሙሉ ታብሌት ቴክኖሎጂ የታገዘ እና 938  መረጃ ሰብሳቢዎች፣208 ሱፐር ቫይዘሮች እና 41 ስታቲሽያኖች በአጠቃላይ 1,187 የሰው ሀይል  በሥራው መሳተፋቸው ታውቋል፡፡

ከጥናቱ የሚገኙት መረጃዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ የሰው ሀይልና ፍልሰት በሚመለከት ለሚዘጋጁት ፖሊሲ ቀረፃና ዕቅድ ግብዓትነት፤ለዘላቂ ልማት ግቦች (SDG) አፈፃፀም ክትትልና ግምገማ የሚውሉ በመሆናቸው ያላቸው ፋይዳ የጎላ ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ የመስክ ሥራው የተጠናቀቀ ሲሆን የጥናቱ ሪፖርት በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ውስጥ ለተጠቃሚዎች ይፋ እንደሚደረግ ከሠራ ክፍሉ ለመረዳት ተችልዋል፡፡