የአዳማ ህንፃ ምረቃ
የአዳማ ህንፃ ምረቃ

በአንድ ዓመት  ጊዜ ግንባታው የተጠናቀቀው የአዳማ ቅ/ጽ/ቤት ህንፃ ተመረቀ

የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ በዓለም ባንክ ድጋፍ ያስገነባው የአዳማ ስታቲስቲክስ ቅ/ጽ/ቤት ህንፃ መስከረም 14/2012 ዓ.ም ተመርቆ በአገልግሎት ላይ ውሏል።

በሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገኝተው ህንፃውን የመረቁት የአዳማ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ መሐመድ ከማል የከተማ አስተዳደሩ የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ የተጣለበትን ታላቅ አገራዊ ኃላፊነት ለመወጣት የሚያደርገው ጥረት እንዲሳካ ከጎኑ እንሚቆም ጠቁመው ለተገነባው ህንፃ የሚያስፈልጉት ግብአቶች እንዲሟሉለት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ  አስታውቀዋል።

የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ተጠሪ ናታሊያ ሚሌንኮ በበኩላቸው በባንኩ ድጋፍ በአዳማ ከተማ የተገነባው ይህ ህንፃ በጥራት፣ በአገነባብና በወሰደው የግንባታ ጊዜ ልዩ እንደሆነ ጠቁመዋል። ተወካይዋ አያይዘውም ህንፃው ውሀና መብራት የመሳሰሉ አገልግሎቶች ተሟልተውለት ለሥራ ዝግጁ በመሆኑ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀው የዓለም ባንክ በቀጣይም ኤጄንሲውን የማዘመን ሥራ በቅ/ጽ/ቤቶች ደረጃም እንደሚሰራበት አስታውቀዋል።

የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢራቱ ይገዙ በበኩላቸው የአዳማው ህንፃ በባንኩ ድጋፍ ከተገነቡት 6 ህንፃዎች ውስጥ አንዱ መሆኑን ገልፀው ከቀደሙት የቅ/ጽ/ቤቶች ግንባታ የተወሰደውን ልምድና ከቅ/ጽ/ቤቱና የከተማ አስተዳደሩ ኃላፊዎች የተሻለ ክትትልና ድጋፍ ተደርጎለት በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ጥራቱ ተጠብቆ የተጠናቀቀ ግንባታ በመሆኑ  ልዩ ያደርገዋል በማለት ገልፀዋል።

የአዳማ ስታቲስቲክስ ቅ/ጽ/ቤት የኦሮሚያ ክልል የሚያከናውነውን ሥራ ለማሳለጥና ተጠቃሚዎች መረጃ በቅርበት እንዲያገኙ እንዲሁም በአካባቢው ለሚገኙት የአዳማና የአርሲ ዩኒቨርስቲዎች እና ሌሎች መሰል ተቋማት ለሚያካሂዱት የምርምር ተግባራት የሚያስፈልጋቸውን መረጃና የማማከር ድጋፍ ለመስጠት የሚያስችል ፋሲሊቲ የተሟላለት ህንፃ መገንባቱን አብራርተዋል።

በአዳማ የተገነባው ህንፃ በቅ/ጽ/ቤቱ የቢሮ አገልግሎት ከመስጠት በተጨማሪ በዋናው መ/ቤት የሚገኘው የተቋሙ የመረጃ ማዕከል /Data Center/ በተለያየ ምክንያት ሊፈጠሩ ከሚችሉት አደጋ የተጠበቀ እንዲሆን ምትክ የመረጃ ማዕከል ሆኖ ማገልገል እንዲችል አስፈላጊው የ ICT ቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት እንሚሟላለት አስታውቀዋል።

በመጨረሻም ዋና ዳይሬክተሩ የህንፃው ግንባታ እንዲሳካ ከፍተኛ ጥረትና ድጋፍ ላደረጉት የቅ/ጽ/ቤቱ ኃላፊ፣ ሠራተኞችና የአዳማ ከተማ አስተዳደር ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የዓለም ባንክ ተወካዮችና የከተማው መስተዳድር ኃላፊዎች፣ የኤጀንሲው ሠራተኞችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።