የኢትዮጵያ ስታቲስቲክ አገልግሎት አመራርና ሠራተኞች ለመከላከያ ሠራዊትና ለተፈናቀሉ ዜጎች የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ

የኢትዮጵያ ስታስቲስቲክስ አገልግሎት አመራርና መላው ሠራተኞች ለሀገር መከላከያ ሠራዊት እና ከሰሜንና ደቡብ ወሎ ተፈናቅሎ ደብረብርሃን ከተማ መጠለያ ለሚገኙ ዜጎች የገንዘብና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ፡፡

እሁድ ህዳር 26/03/2014 ዓ.ም በደብረብርሃን ከተማ ተገኝቶ ከሰሜንና ደቡብ ወሎ ለተፈናቀሉ ዜጎች በተቋሙ ሠራተኞች የተሰበሰበውን የአልባሳትና ምግብ ቁሳቁስ ድጋፍ ለዞኑ ያስረከቡት የአገልግሎቱ ም/ዋና ዳይሬክተር ወ/ሪት አበራሽ ታሪኩ አሸባሪው የትህነግ ቡድን በአማራና አፋር ክልሎች ባደረገው መጠነ ሰፊ ወረራ ባደረሳቸው የሰበአዊና ቁሳዊ ውድመት በፅኑ የምንቃወም መሆናችንን  እየገለፅን በዚህ ወረራ ካለሀጥያታቸው ከቄያቸው ለተፈናቀሉና የተጎዱ ዜጎቻችን ላይ የደረሰው ከፍተኛ ጉዳት የእነሱ ብቻ ሳይሆን የሁላችንም ኢትዮጵያዊ ጉዳት መሆኑን መላው አመራርና ሠራተኞች በፅኑ እንደሚገነዘቡ አስረድተዋል፡፡

በዚሁ መነሻ በሀገራችን ላይ በውስጥና በውጭ ፀረ ኢትዮጵያ አንድነት ሀይሎች የተከፈተብን ጦርነት ለመቀልበስ የሚደረገው ጥረት ለማገዝ የተቋሙ ሠራተኞችና አመራር ለመከላከያ ሠራዊቱ ደም ከመለገስ በተጨማሪም ሠራዊቱን በፋይናንስ ለማጠንከር በዋና መ/ቤት እና በ25ቱ የስታተስቲክ /ቅ/ጽ/ቤት የሚገኙት ሠራተኞች የአንድ ወር ደሞዛቸውን በድምሩ 9,095,796.98 /ዘጠኝ ሚሊየን ዘጠና አምስት ሺ ሰባት መቶ ዘጠና ስድስት/ ብር ድጋፍ፣የተደረገ ሲሆን ለተፈናቀሉ ዜጎች በመጀመሪያ ዙር በተቋማችን ዋና መ/ቤትና አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚገኘው የአ.አ ስታቲስቲክ ቅ/ጽ/ቤት ሠራተኞች በጋራ ሆነው የሰበሰቡትን ድጋፍ በአማራ ክልል ሰሜንና ደቡብ ወሎ ተፈናቅለው በደብረብርሃን ከተማ መጠለያ ለሚገኙት ዜጎቻችን ከአዋቂ እስከ ህፃናት የሚጠቀሙበት የተለያዩ አልባሳቶችን እና የሴቶች ንፅህና መጠበቂያ ግምታቸው ብር 2,056,575.96 እና ለምግብነት የሚውሉ ግምታቸው ብር 204,608 በድምሩ 2,261,183.96 የሚገመት ድጋፍ ለዞኑ አስረክበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ተቋም አመራርና ሠራተኞች በሀገራችን ላይ በውስጥ ባንዳዎችና በጋላቢዎቻቸው የምዕራባዊያን ኃያላኖች የተከፈተብን መልከ ብዙ ጦርነት ለመቀልበስ እስከ አሁን 11,356,979.96/ አስራ አንድ ሚሊየን ሦስት መቶ ሃምሳ ስድስት ሺ ዘጠኝ መቶ ሰባ ዘጠኝ ከዘጠና ስድስት ሳንቲም/ ብር ድጋፍ ያደረጉ ሲሆን በቀጣይም የተከፈተብንን ጦርነት ሀገራችን መንግስትና ህዝብ ጠንካራ አንድነት ድል እስከሚሆን ድረስ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ማድረጉን ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑ ም/ዋና ዳይሬክተሯ ገልፀዋል፡፡

ድጋፉን ከአገልግሎቱ ም/ዋና ዳይሬክተር የተረከቡት የሰሜን ሸዋ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አበበ መሰለ የተቋሙ ሠራተኞች እና አመራር ያደረጉት ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበው ወረራውን ለመመከት የዜጎቻችን አንድነት ና ድጋፍ በጣም አስፈላጊ በመሆኑ ድጋፍ በሁሉም ግንባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጽዋል፡፡