የደሴ ህንፃ ምረቃ
የደሴ ህንፃ ምረቃ

የደሴ ቅ/ጽ/ቤት አዲስ ህንፃ ተመረቀ

በዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ የተገነባው የደሴ ቅ/ጽ/ቤት አዲስ ህንፃ መስከረም 18/2012 ዓ.ም ተመርቆ ለአገልግሎት በቅቷል።

የደሴ ከተማ ከንቲባ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍስሀ ጥላሁን በህንፃው ምርቃት ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ለሀገራችን የልማትና የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ዕቅድ፣ ፖሊሲና ስትራቴጂ ቀረፃ፤ ክትትልና ግምገማ የሚያስፈልጉትን የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የሥነ ሕዝብ ስታቲስቲካዊ መረጃዎችን በማቅረብ ላለፉት አምስት አስርታት ለታየው አገራዊ ለውጥ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ያለ አንጋፋ ተቋም መሆኑን ገልፀው ኤጀንሲው ይበልጥ ተጠናክሮ አገራችን የሚያስፈልጋትን መረጃ በወቅቱና በጥራት ማቅረብ እንዲችል ምንም እንኳን  የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የመሬት አቅርቦት ችግር ቢኖርበትም ከስታቲስቲክስ መረጃዎች ከሚገኘው ጥቅም ስለማይበልጥ ከ1500 ካሬ ሜትር በላይ መሬት ለህንፃ ግንባታው በመስጠት  ዕገዛ ማድረጉን አስታውሰው በቀጣይም ኤጀንሲው ስታቲስቲክስን ለማዘመን በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ሁሉ አስተዳደራቸው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢራቱ ይገዙ በበኩላቸው ኤጀንሲው የተለያዩ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የስነህዝብ መረጃዎችን በመሰብሰብ፣ በማጠናቀርና በመተንተን ለተጠቃሚዎች የሚያቀርብባቸው 25 ቅ/ጽ/ቤቶች እንዳሉት አስታውሰው በሁሉም ቦታዎች የራሱ ህንፃ ስለሌለው ከግለሰቦችና የተወሰኑትን ከመንግሥት በመከራየት ሲጠቀም ቢቆይም የኪራይ ዋጋ እየናረ መሄድና አከራዮች በየጊዜው እያስለቀቁት የተዘረጉ የዳታ ኔትወርክ በማፍረስ ለከፍተኛ ወጪ ከመዳረጉም በላይ ለመረጃ ተጠቃሚዎች ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት ሲቸገር ቆይቷል።

እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ከዓለም ባንክ ጋር ተከታታይ ውይይት በማካሄድ በባንኩ ድጋፍ በባህርዳር፣ በመቀሌ፣ በሀዋሳ፣ በአምቦ፣ በአዳማና በደሴ የቢሮ ህንፃዎች መገንባታቸውን አስታውሰው ባንኩ በሁሉም የልማት ዘርፎች ለአገራችን ከሚያደርገው ድጋፍ ባሻገር የሀገሪቱን የስታቲስቲክስ አቅም ለማሳደግና ለማዘመን ተከታታይ እገዛ እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

በመጨረሻም ዋና ዳይሬክተሩ ለክልሉ መንግሥት፣ የከተማው አስተዳደር እና ህንፃው የተገነባበት መንደር ነዋሪዎች የስታቲስቲክስ መረጃ ለልማት ሥራዎች ያላቸውን ከፍተኛ ጠቀሜታ በመረዳት ለህንፃ ግንባታ የሚውለውን ቦታ በነፃ በመስጠትና ግንባታው በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ላደረጉት ትብብር እና ዕገዛ ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።