በተቋሙ አዲስ አደረጃጀት ላይ ውይይት ተደረገ

ኤጀንሲው ከፍተኛ፣ መካከለኛና ቅ/ጽ/ቤት ሃላፊዎች በተገኙበት በኤጀንሲው አዲሱ ተግባርና ሀላፊነት እንዲሁም ስያሜ ላይ ህዳር8/0213ዓ.ም በአዳማ ከተማ ከፕላንና ልማት ሚኒስቴር ዴኤታ ዶክተር ነመራ ገበየሁ ጋር ውይይት ተካሄደ፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የተወካዮች ምክር ቤት ስድስተኛ ዙር የመጀመሪያ ስራ ዓመት መስከረም26/0213ዓ.ም በተደረገው ስብሰባ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ መንግስት ተቋማት እንደገና ለማደራጀት የተዘጋጀው አዲስ አደረጃጀት በምክር ቤቱ መጽደቁ ይታወቃል፡፡

እንደገና በአዋጁ ከተቋቋሙት ተቋማት መካከል አንዱ የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ሲሆን በዚህ አዋጅ የተቋሙ ተግባርና ሀላፊነት የነበረው ብሔራዊ ስታቲስቲክስ ጥራትና ደረጃ ተግባራትን የማስተባበር ሃላፊነት የመረጃ ጥራትን የመቆጣጠር ስልጣን በመሆኑ ኤጀንሲው መረጃ የማመኝጨት ተግባሩ ላይ ትኩረት እንዲያደርግ ታስቦ ወደ ፕላንና ልማት ሚኒስቴር ተወስዷል፡፡ እንዲሁም ማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ተብሎ ሲጠራበት የነበረው ስያሜም ተቀይሮ በአዲሱ አዋጅ የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት እንዲሆን የተደረገው መንግስት አሁንና ወደፊት የሚኖረውን የመረጃ ክፍተት በተሟላ መልኩ ለመሙላት የሚያስችል ተቋማዊ ቁመናና ስያሜ እንዲኖረው ተፈልጎ እንደሆነ ሚኒስቴር ዴኤታው ዶ/ር ነመራ ገበየሁ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ገለጻ አስረድተዋል፡፡

ለተቋሙ የተሰጠው አዲስ ተግባርና ሃላፊነት፣ የስያሜ ትርጉም እንዲሁም ደረጃውን በተመለከተ ከአዋጁ መጽደቅ በኋላ ከአመራሩና መላው ሰራተኛ ጋር ጥያቄ የሚፈጥሩና ግልጽነት በሚፈልጉት ጉዳዮች ላይ አመራሩ ሰፊ ጥያቄ አንስቶ በሚኒስቴር ዴኤታው ምላሽ የተሰጠበት ሲሆን በተለይም ከተቋሙ ስያሜ ጋር ተያይዘው የተቋሙ ደረጃ ይወርዳል በሚል የተፈጠረው ስጋት ተገቢ እንዳልሆነ የተቋሙ ደረጃ ከስያሜው ጋር የሚያገናኘው ምንም ነገር እንደሌለ በመግለጽ ምላሽ የሰጡት ሚኒስቴር ዴኤታው ሌሎች የተነሱት ቴክኒካዊ ጉዳዮች እንዲሁም አሁን በዚህ አዋጅ ያልታዩ ነገሮች የተነሱትን ጥያቄዎች እንደግብአት በመውሰድ በቀጣይ ባለው አሰራር እየታዩ ምላሽ የሚሰጣቸው እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡

በዕለቱ በውይይት መድረኩ ላይ ተገኝተው በመጨረሻ የስራ መመሪያ የሰጡት የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢራቱ ይገዙ የተሰጡንን ተግባራትና ሃላፊነት በተገቢው መልኩ እየሰራን መስተካከል ያለባቸው ጉዳዮች በሂደት መልስ እንዲያገኙ መስራት እንደሚገባ፤ በዚሁ መሰረት በተቋሙ አዲሱ ተግባር፣ ሃላፊነትና ስያሜ ላይ ያገኛችሁትን ግንዛቤ በሥራ ክፍላችሁና በቅ/ጽ/ቤቶቻችሁ ሠራተኞች በማስረዳት ስራቸውን በአዲስ መንፈስና ከስጋት ነፃ በሆነ ሁኔታ እንዲሰሩ ማድረግ እንደሚገባቸው ገልጸዋል፡፡

በዚህ የውይይት መድረክ ከዋና መ/ቤትና 25 ቅ/ጽ/ቤቶች የተወጣጡ 50 አመራሮች ተሳትፈውበታል፡፡