የመስከረም ወር የዋጋ ግሽበት 2012

የምግብ ዋጋ በመስከረም ጭማሪ አሳይቷል

የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ በየወሩ የሚያወጣው የዋጋ ግሽበት ሁኔታ መረጃ በመስከረም  2012 ዓ.ም የተመዘገበው አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ከመስከረም 2011 ዓ.ም ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነፇፃፀር በ18.6 ከመቶ ከፍ ብሎ ታይቷል። የዋጋ ግሽበት ሁኔታ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር በማነፃፀር የሚገኘው ውጤት ወቅታዊ የዋጋ ግሽበት ሁኔታን የሚያሳይ ሲሆን ከዚህም ውስጥ የምግብ ዋጋ ግሽበት የመስከረም ወር 2012 ዓ.ም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነፃፀር በ23.3 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። ዋና ዋና የእህል ዓይነቶች (በተለይ ጤፍ፣ ገብስ፣ ማሽላ፣ በቆሎና የስንዴ ዱቄት) ዋጋ ጭማሪው በዚህም ወር የቀጠለ ቢሆንም የአጨማመሩ ፍጥነት ግን ካለፉት ወራት ያነሰ ነው። ከዚህ በተጨማሪም በየቀኑ ለምግብነት ተፈላጊ የሆኑት አንዳንድ የአትክልት ዓይነቶች በተለይም ቲማቲም፣ ቀይ ሽንኩርትና ነጭ ሽንኩርት በአንድ ወር ውስጥ ጭማሪ በማሳየታቸው የዋጋ ግሽበት ከፍ እንዲል አስተዋፅኦ አድርጓል።

በሌላ በኩልም ምግብ ነክ ያልሆኑ የኢንዴክሱ ክፍሎች የዋጋ ግሽበት የመስከረም ወር 2012 ዓ.ም ካለፈው ዓመት መስከረም ወር 2011 ዓ.ም ጋር ሲነፃፀርም የ13.1 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። ካለፉት ጥቂት ወራት ጀምሮ ምግብ ነክ ያልሆኑ የኢንዴክሱ ክፍሎች የዋጋ ግሽበት በተከታታይ ጭማሪ እያሳየ ነው። ምግብ ነክ ያልሆኑ የኢንዴክሱ ክፍሎች የዋጋ ግሽበት ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከፍ እንዲል ካደረጉት ዋና ምክንያቶች ውስጥ በተለይ ልብስና መጫሚያ፣ የቤት ኪራይ፣ የቤት እንክብካቤና ኢነርጂ (ማገዶና ከሰል)፣ የቤት ዕቃዎችና የቤት ማስጌጫዎች፣ የቤት መስሪያ ዕቃዎች፣ ህክምና እና ትራንስፖርት (በተለይ የቤት መኪና) ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ ነው።

በአጠቃላይ በመስከረም ወር 2012 ዓ.ም በ18.6 በመቶ ከፍ ብሎ ለታየው የዋጋ ግሽበት ዋነኛ ምክንያት ሆኖ የተገኘው የመስከረም ወር በኢትዮጵያ የአዲስ ዓመት መግቢያ ወቅት በርካታ በዓሎች ስለሚከበሩበት ነው።

ለተጨማሪ መረጃ

አቶ አለማየሁ ተፈሪ የቤተሰብ ጥናቶችና ዋጋዎች ስታቲስቲክስ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ስልክ ቁጥር 0922397174

አቶ ሳፊ ገመዲ የሕዝብ ግንኙነትና መረጃ ሥርጭት ዳይሬክቶሬት የስልክ ቁጥር ሞባይል 0911549537- የቢሮ 0111564226

For more information about monthly inflation data please use our web site www.statsethiopia.gov.et  

ሠንጠረዥ መ:  የዘንድሮውና የአምናው ተመሳሳይ ወሮች የሸማቾች ዋጋ ኢንዴክስ ለውጥ ንጽጽር በአገር አቀፍ ደረጃ

Table D: Summary of Comparison of CPI Movements, Current vs. Last year’s Similar Months at Country Level