የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ የኮንስትራክሽን ሥራ እንቅስቃሴ ጥናትን በማካሄድ ላይ ነው

የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ የኮንስትራክሽን እንቅስቃሴ ጥናትን በመላው ሀገሪቱ በማካሄድ ላይ ነው፡፡

የኮንስትራክሽን ስራ እንቅስቃሴ ጥናት ከአንድ አመት በላይ አገልግሎት የሚሰጡ ንብረቶችን ለመገንባት፣ ለማደስ እና ለመጠገን የሚካሄድ የስራ እንቅስቃሴ ላይ ያተኮረ ሲሆን ጥናቱ ሕንፃዎችን፣ ድልድዮችን፣ የውሃ መውረጃ ትቦዎችን፣ የውሀና የኤሌክትሪክ መስመሮችን፣ የአውሮፕላን ማረፊያዎችን፣ የመኪና ማቆሚያዎችን፣ ግድቦችን፣ የውሃ ጉድጓዶችን፣ የመገናኛ መስመሮችን፣ የወደብ ሥራዎችን፣ የማዕድን፣ የነዳጅና የተፈጠሮ ጋዝ ቦታዎችን የማዘጋጀት የመገንባት የመቆፈርና ሌሎችም ተመሳሳይ ዘርፎችን የመገንባት፣ የማፍረስ፣ የመለወጥ፣ የማደስና የመጠገን የስራ ሂደቶችን ሁሉ ያጠቃልላል፡፡

የጥናቱ አላማም በኮንስትራክሽን ዘርፍ በመላ ሀገሪቱ የሚደረግ እንቅስቃሴ በአጠቃላይ ኢኮኖሚው በምን ዓይነት እርምጃ እየሄደ ስለመሆኑ፤ ዘርፉ ለሀገር ሀብት (GDP) ያለውን አስተዋፅኦና የደረሰበትን ደረጃ ለማሳየት የሚያስችሉ የኮንስትራክሽን ስታቲስቲክስ መረጃዎችን ማስገኘት ሲሆን ዘርፉ ለሀገር ሀብት ውጤት የሚያበረከረተውን ድርሻ ለማስላት አስፈላጊ መረጃም ያስገኛል፡፡

ጥናቱ በ2,924 ድርጅቶች ላይ የሚካሄድ ሲሆን በ300 መረጃ ሰብሳቢዎች፣ 71 ተቆጣጣሪዎች እና በ28 ስታቲስቲሺያኖች ይካሄዳል፡፡ እንዲሁም ከዋናው መ/ቤት የቢዝነስ ስታቲስቲክስ ዳይሬክቶሬት በተላኩ ባለሞያዎች ቁጥጥር እና ድጋፍ በመላ የሀገሪቱ ክልሎች በተሰራጩ ፕሮጀክቶች አማካይነት የሚካሄድ ሲሆን መረጃዎች በወረቀትና በታብሌት ቴክኖሎጂ ይሰበሰባሉ፡፡

በጥናቱ የዘርፉን አጠቃላይ እንቅስቃሴ የሚመለከቱ፣ ለምን ያህል ዜጎች የሥራ ዕድል እንደተፈጠረ፣ የተሰሩ ስራዎች በገንዘብ መጠን፣ የተጠቀሙትን የኮንስትራክሽን ግብአቶች፣ የሚያንቀሳቅሰው ካፒታል መጠንና፣ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት የሚያበረክተው ድርሻ የሚጠቁሙ መረጃዎች ይሰበሰባሉ፡፡ ከጥናቱ የሚገኙ መረጃዎችን በዋነኝነት መንግስት ዘርፉን ለማሳደግ ለሚያወጣቸው ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች፣ የኢኮኖሚ ፖሊሲና የልማት ዕቅድ አውጪዎች እንዲሁም ለዘርፉ ባለቤቶች እንደቁልፍ ግብአት ያገለግላል፡፡