የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ ልማት ፕሮግራም ይፋ ተደረገ

   ጥር 23/2016 ዓ.ም የቀጣይ ሶስት ዓመታት (2016-2018) የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ ልማት ፕሮግራም (Ethiopian statistical development program – ESDP) የሀገር ውስጥና የውጭ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል ይፋ አደረገ፡፡

በዚህ ፕሮግራም ላይ ከሁሉም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ አለም አቀፍ ተቋማት የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉ ሲሆን ዶ/ር ፍፁም አሰፋ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር በፕሮግራሙ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር በስታቲስቲክስ ልማት ላይ የሚደረገው ማንኛውም ኢንቨስትመንት የሀገራችንን የነገውን መፃኢ እድል በተገቢ መንገድ ማየት የሚያስችለን ነው ሲሉ ገልፀው፣ ዛሬ ይፋ የምናደርገው ሀገራችን በቀጣይ ሶስት ዓመታት በስታቲስቲክስ ዘርፍ በሰው ሀይል፣ በቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ መረጃ የመሰብሰብና የማቅረብ አቅምን ለማሳደግ፣ የስታቲስቲክስ ሜቶዶሎጂን ለማሻሻልና ለማዘመን፣ የመሰረተ ልማት ግንባታን ለመተግበር እንዲቻል በአጠቃላይ 34.7 ቢሊየን ብር የሚጠይቅ የልማት ፕሮግራም የተያዘ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ስለሆነም መንግስት የዘርፉን የልማት ፕሮግራም ለመደገፍ ከፍተኛ ቁርጠኝነት ያለው ቢሆንም ብቻውን የሚወጣው ባለመሆኑ በፕሮግራሙ ላይ የተሳተፋችሁ አጋር አካላት አስፈላጊውን ድጋፍ እንድታደርጉ ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

በልማት ፕሮግራሙ የሚከናወኑ ዝርዝር ተግባራትን በሚመለከት በኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር በከር ሻሌ ገለፃ ቀርቦ በፕሮግራሙ ተሳታፊዎች ሰፊና ጠቃሚ ውይይት ተደርጎበታል፡፡