የወሳኝ ኩነት መረጃን የማቀነባበር ተግባር በቅ/ጽ/ቤቶች ሊጀመር መሆኑ ተገለጸ

በስታቲስቲክስ ቅ/ጽ/ቤቶች የወሳኝ ኩነት መረጃ ማቀናበር የሚችል የሰው ሀይልን በማዘጋጀት ላይ ያተኮረ ስልጠና ከታህሣሥ 07-09/2012ዓ.ም በዋናው መ/ቤት የስልጠና ማዕከል ተሰጠ፡፡

የኤጀንሲው የስነህዝብ እና ቫይታል ስታቲስቲክስ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አሳልፈው አበራ በስልጠናው መክፈቻ ንግግራቸው የስልጠናው ዋነኛ አላማ በስታቲስቲክስ ቅ/ጽ/ቤት የወሳኝ ኩነት መረጃ ማቀናበር የሚችል የሰው ሀይል ማዘጋጀት እንደሆነና በስልጠናውም የፌደራልና የክልል ባለሞያዎች ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የወሳኝ ኩነት ምዝገባ እና የስታቲስቲክስ ስርአት በሀገራችን ከሀምሌ 2008 ጀምሮ በመካሄድ ላይ መሆኑን አይይዘው ያስታወሱት ም/ዋ/ዳሩ ይህ ስርአት መጀመሩ ለሀገር ልማት እና እድገት ብሎም ለዜጎች ተጠቃሚነት የሚኖረው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ የዜጎችን የፍትህ፣ አስተዳደርና የሰብአዊ መብት ጉዳዮች እንዲሁም በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚና በፖለቲካ ዘርፍ አገልግሎት እንደሚያስገኝ፤ በስታቲስቲክስ ረገድም የህዝብ ዕድገትን ለመተንበይ፣ የውልደት መጠንን፣ የሞት ምጣኔን እና ምክንያቶችን፣ የጋብቻና ፍቺ መረጃዎችን በሪፖርት መልክ ለማውጣት ጠቃሚ እንደሆነም አብራርተዋል፡፡

ኤጀንሲው ከቆጠራ፣ ከናሙና ጥናቶች፣ ከማያቋርጥ ምዝገባ (የወሳኝ ኩነት ምዝገባና) ከአስተዳደር መዛግብት ጥራታቸውን እና ወቅታዊነታቸውን የጠበቁ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ሥነ-ህዝብ መረጃዎችን በተቀናጀ መልኩ በመሰብሰብ፣ በማጠናቀርና በመተንተን ውጤቱን ለተጠቃሚዎች የማቅረብ ሀላፊነት በአዋጅ 442/1997 እንደተሰጠው ያስታወሱት ም/ዋ/ዳሩ ከሌሎች ምንጮች የሚገኘውን መረጃ በማጠናቀር ለተጠቃሚዎች የማቅረቡ ስራ በሰፊው እየተካሄደ ቢገኝም ከወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ በመዘግየቱ መረጃ ማቅረብ እንዳልተቻለ ገልጸዋል፡፡

በዋናው መ/ቤት ባለፉት አመታት  ሲካሄድ የነበረው የወሳኝ ኩነቶች መረጃን የማደራጀት፣ የእርማትና መለያ መስጠት፣ የማቀነባበር ስራ በቀጣይ በቅ/ጽ/ቤቶችም የሚጀመር መሆኑን ለስራው መሳካትም የተለያዩ ቅድመ ዝግጅት ስራዎች በመካሄድ ላይ መሆናቸውን ለዚህም ሲባል ሥራው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በስልጠናው ላይ የተገኙ ባለሞያዎችም ስልጠናውን በአግባቡ እንዲከታተሉና ከስልጠናው በኋላም ለስራው መሳካት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

በስልጠናው የቫይታል ስታቲስቲክስ ስርአትና ምንነት፣ የመረጃ ምንጮችና መርሆች፣ የቫይታል ስታቲስቲክስ መረጃምንጮችና ንጽጽር፣ መረጃው የሚያስገኛቸው ጥቅሞች፣ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ስርአትና ምንነት የሚሸፍኑት የመረጃ ዓይነቶችና መሰረታዊ መርሆቹ፣ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ አስፈላጊነትና የሚያስገኛቸው ጥቅሞች፣  የቫይታል ስታቲስቲክስ መረጃ ኤዲቲንግ እና ኮዲንግ፣ የልደት የሞት የጋብቻና ፍቺ ክብር ቅጽ አያያዝ ላይ ያተኮሩ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡

በስልጠናው ላይ የፌደራል እና የክልል ወሳኝ ኩነት ምዝገባ ኤጀንሲ ባለሞያዎች፣ የስታቲስቲክስ ቅ/ጽ/ቤት ሀላፊዎች እና ባለሞያዎች እንዲሁም የዋናው መ/ቤት የቫይታል ስታቲስቲክስ ባለሞያዎች የተሳተፉ ሲሆን የወሳኝ ኩነት መረጃን የማቀናበር ሥራም በቅ/ጽ/ቤቶች ደረጃ በጥርና በየካቲት 2012ዓ.ም ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በመጨረሻም ለስልጠናው ድጋፍ ላደረገው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሥነ-ህዝብ ፈንድ ምስጋና አቅርበዋል፡፡