የወሳኝ ኩነት ምዝገባ እና የቫይታል ስታቲስቲክስ ስርዓት ላይ ስልጠና ተሰጠ

የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ከክልልና ከፌደራል ኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት፣ ከስታቲስቲክስ ቅ/ፅ/ቤትና ከዋናው መ/ቤት ለተውጣጡ ባለሞያዎች በወሳኝ ኩነት ምዝገባና የኩነቶች ስታቲስቲክስ ፅንሰ ሀሳብ ዝርዝር የአሰራር ሄደቶች፣ በእርማትና መለያ አሰጣጥ መመሪያ እንዲሁም የመረጃ ቅብብሎሽና አጠባበቅ ዙርያ ከህዳር 21 እስከ 24/2014 ዓ.ም በአዳማ ፓናፍሪክ ሆቴል ስልጠና ተሰጠ፡፡

ስልጠናውን በንግግር የከፈቱት የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የስነ-ሕዝብና ቫይታል ስታቲስቲክስ ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ አሳልፈው አበራ በንግግራቸው እንደገለፁት ከኢሚግሬሽንና ዜግነት አግልግሎት ተመዝግበው የሚመጡ ኩነቶች ለስታቲስክስ ስራ የሚውሉ መረጃዎችን በመለየት በመተንተና በማጠናቀር ለተጠቃሚዎች ሪፖርት ለማውጣት ተቋማቸው እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ የወሳኝ ኩነት የሚካሄድባቸው ኩነቶች /ልደት፣ ጋብቻ፣ ፍቺ፣ ሞት፣ ጎድፌቻና ሌሎች በሰው ልጆች ላይ የሚከሰቱ ኩነቶች/ የመመዝገብ ስርዓት እየተከናወነ በመሆኑ እነዚህ ኩነቶች ተመዝግበውና ተደራጅተው ለህግ፣ ለአስተዳደር ጉዳዮችና ለስታቲስቲክስ አገልግሎት የሚውሉ ሲሆኑ ከወሳኝ ኩነት ምዝገባ የሚገኘው የቫይታል ስታቲስቲክስ መረጃዎች የህዝብ ቁጥርን ለመተንበይ፣ የልደትና የሞት መጠን መረጃዎችን ለማግኘት፣ ለሞት መንስኤ የሆኑ ምክንያቶችን መረጃ ለማግኘትና የጋብቻና የፍቺ ቁጥር መረጃ ለማግኘት እንደሚጠቅም ተገልጿል።

የወሳኝ ኩነት ምዝገባ እየተካሄደ የሚገኘው በወረቀት በመሆኑ የጊዜና መረጃዎች በትክክል ፎርሙ ላይ ያለመሞላት ችግሮች የሚያጋጥሙ ሲሆኑ ችግሮቹን ለመቅረፍም የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በሚቀጥሉት አምስት አመታት የምዝገባ ስርዓቱ ወደ ዲጅታል ለመለወጥ በአዲስ አበባና በአንዳንድ የክልል ከተሞች የሙከራ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡

ከወሳኝ ኩነት ወደ ስታቲስቲክስ የሚመጡ ኩነቶች በምዝገባ ወቅት የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመቅረፍ የወሳኝ ኩነትና የስታቲስቲክስ ተቋም በጋራ በመወያየት በቀጣይ የተሻለ ስራዎችን ለመስራት ያለመ የስልጠና መድረክ ሲሆን የማህበረሰቡን ግንዛቤና የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ሽፋን ለማሳደግ የሚያስችል ስራዎች ለመስራት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተጠቅሷል፡፡

ከስልጠናው ተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የተነሱ ሲሆን የስነ-ሕዝብና ቫይታል ስታቲስቲክስ ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ አሳልፈው አበራ በስልጠናው መዝጊያ ላይ ይህ ስራ በጋር የሚሰራ ስራ በመሆኑ በቀጣይ ሁለቱ ተቋማት በጋራ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ስልጠናው ከዋናው መ/ቤትና ቅ/ጽ/ቤቶች ለተውጣጡና የዳታ ኢንትሪ፣ ዳታ ክሊኒንግ፣ ኤዲተሮችና የዶክመንቴሽን ባለሙያዎችና ከኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ለመጡ 135 ባለሞያዎችና ሀላፊዎች ስልጠናው የተሰጠ ሲሆን በስልጠናው የተሳተፉት ባለሙያዎችም በቂ ግንዛቤ የተገኘበት ስልጠና እንደሆነ ከሰልጣኞቹ ሀሳብ ለመረዳት ተችሏል፡፡