የዋናው መኸር የሰብል ምርት መጠን ከአምናው ጭማሪ እንዳለው ተተነበየ

በ2012ዓ.ም በዋናው መኸር ወቅት በአነስተኛ የግል ገበሬዎች በሚኖረው የሰብል ምርታማነት በሁሉም የሰብል ዓይነቶች (በብርዕና አገዳ፣
በጥራጥሬ እና ቅባት ሰብሎች) በሚመደቡ ዋና ዋና ሰብሎች የሚኖረው ምርታማነት በ2011 ከነበረው ምርታማነት ጋር ሲወዳደር እንደሚጨምር
ተተነበየ፡፡

ይህ የተተነበየው ታህሳስ 30/2012 ዓ.ም የዋናው መኸር ወቅት የአነስተኛ የግል ገበሬዎች ቅድመ ሰብል ምርት ትንበያ ናሙና ጥናት ዋና ዋና ግኝቶችን በተመለከተ የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢራቱ ይገዙ በፅ/ቤታቸው ለሀገር ውስጥ ጋዜጠኞች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡

ከዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ ለመረዳት እንደተቻለው በ2012 ዓ.ም በዋናው መኸር ወቅት የሰፋፊና መካከለኛ የንግድ እርሻዎችን፣ የበጋ ወቅት መስኖ እና
የበልግ ወቅት እርሻዎችን ምርት ሳያካትት በአነስተኛ የግል ገበሬዎች ብቻ ታርሶ በዋና ዋና የምግብ ሰብሎች የተሸፈነ መሬት ስፋት ግምት 12,773,911.58 ሄክታር ሲሆን በሰብል ዘመኑ ሊገኝ ይችላል ተብሎ የሚጠበቀው የምርት መጠን 329,281,366.98 ኩንታል ነው፡፡

ሠንጠረዥ 1. በ2012 መኽር ወቅት የታረሰ መሬት ስፋትና ሊገኝ ይችላል ተብሎ የሚጠበቅ ምርት መጠን በሰብል ዓይነት

የሰብል ዓይነት በሰብል የተሸፈነ መሬት ስፋት በሄክታር % ሊመረት ይችላል ተብሎ የሚጠበቅ የምርት መጠን በኩንታል %
ብርዕና አገዳ እህሎች 10,421,645.78 81.59 291,090,949.29 88.40
ጥራጥሬ 1,576,175.26 12.34 30,027,095.89 9.12
የቅባት እህሎች 776,090.54 6.08 8,163,321.81 2.48
ጠቅላላ ሰብል 12,773,911.58 100.00 329,281,266.98 100.00

በ2012 ዓ.ም የመኸር ወቅት ከአነስተኛ የግል ገበሬዎች ብቻ እንደሚገኝ የሚጠበቀው የምርት መጠን ከአምና (2011 ዓ.ም.) መኸር ወቅት ምርት ጋር ሲነጻጸር የ4.33 በመቶ ወይም ወደ 13.7 ሚሊዮን ኩንታል ጭማሪ እንደሚያሳይ ይጠበቃል፡፡

ከምግብ እህሎች የብርዕ እና አገዳ እህሎች 4.85 በመቶ ዕድገት እንደሚያሳዩ ከዚህም ጤፍ፣ ስንዴ፣ በቆሎና ማሽላ ጭማሪ እንደሚያሳዩ ተተነበየ፡፡በዘንደሮው መኸር ወቅት የጥራጥሬ ሰብሎች ምርት አምና ከተገኘው ምርት ጋር ሲወዳደር በመጀመሪያ ግምት መረጃ መሰረት አተር፣ ነጭ አደንጓሬ፣

ምሥር፣ ጓያ፣ አኩሪ አተር፣ ማሾ እና ግብጦ ጭማሪ እንደሚያሳዩ የየተነበየ ሲሆን በቀሪዎቹ የጥራጥሬ ሰብሎች ምርት በመጀመሪያ ግምት
ትንበያ መሰረት ብዙም ለውጥ አልታየም፡፡ የቅባት ሰብሎች ምርት አምና ከተገኘው ምርት ጋር ሲወዳደር የ3.99 በመቶ ጭማሪ እንደሚያሳይ የሚጠበቅ ሲሆን በተለይም የሰሊጥና የለውዝ ምርት የተሻለ ጭማሪ እንደሚያሳዩ ከሪፖርቱ መገንዘብ ተችሏል፡፡

የጥናቱ መረጃዎች ወካይ ከሆኑና በሳይንሳዊ መንገድ ከመላ ሀገሪቱ በተመረጡ 2,815 ናሙና የጥናት ቦታዎች ውስጥ ኗሪ ከሆኑና
56,300 ቤተሰቦች ውስጥ ከሚገኙ በዘንድሮው የመኸር ወቅት ሰብል በማምረት ሥራ ተሰማርተው ከነበሩ ባለይዞታ ገበሬዎች የተሰበሰቡ
ሲሆን በመስኖም ሆነ በሌላ ዘዴ የተዘሩትን የግብርና ምርቶች አላካተተም፡፡