UNFPA ለኤጀንሲው የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚቀጥል አስታወቀ

አዲሷ የUNFPA በኢትዮጵያ ካንትሪ ዳይሬክተር ወ/ት ዴሊያ ጄልና የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ከፍተኛ አመራሮች የካቲት 11/2013ዓ.ም በዋና ዳይሬክተር የስብሰባ አዳራሽ ትውውቅ አደረጉ።

በትውውቅ መድረኩ ካንተሪ ዳይሬክተሯ UNFPA ከኤጀንሲው ጋር ለረጅም ጊዜ የቆየ አጋርነት እንዳለው፤ የኢትዮጵያ ህዝብና ቤት ቀጠራና ሌሎች ጥናቶች ላይ ከፍተኛ ድጋፍ እንዳደረገ በዚህም ደስተኛ እንደሆኑ ገልጸው አሁን እየተሰሩ ላሉ የተቀናጀ የመረጃ ተደራሽነት ስርዓት(IMIS)፣ የዜግነትና ወሳኝ ኩነት ምዝባ (CRVS)፣ የኢትዮጵያ ስነ-ህዝብና ጤና ጥናትና ሌሎችም ወደፊት ለታቀዱ ጥናቶች ድጋፋቸው እንደሚቀጥል አስረድተዋል፡፡

የኤጀንሲው ከፍተኛ አመራሮች UNFPA ለረጅም ጊዜ ለነበረው ጠንካራ አጋርነትና ላበረከተው የቴክኒክና ፋይናንስ ድጋፍ ያላቸውን ከፍተኛ ምስጋና ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም በተቋሙ ውስጥ የሚካሄዱትን ስትራቴጂክ የሆኑ፤ የብሄራዊ ስታቲስቲክስ ስርአቱን ማጠንከር እና የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ተግባራት ላይ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ካንትሪ ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡