የ2013ዓ.ም የበልግና መስኖ እርሻ ናሙና ጥናትን ለማስጀመር የሚያስችል ስራ እየተሰራ ይገኛል

የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ የ2013ዓ.ም የበልግ እርሻና የበጋ ወቅት መስኖ እርሻ ናሙና ጥናትን ለማካሄድ ከየካቲት 08-16/2013 ዓ.ም በአዳማ፣ ሀዋሳ፣ ጅማ፣ ባህርዳርና አምቦ በሚገኙ ማዕከላት ለ166 አሰልጣኝ ስታቲስቲሺኖች ስልጠና ሰጠ፡፡

ከበልግ ወቅት እርሻ ናሙና ጥናት የሚሰበሰቡ ዋና ዋና መረጃዎች በወቅቱ ያለው የዘር አጠቃቀም፣ የመስኖ አጠቃቀም በሰብል ዓይነት፣ የማዳበሪያ አጠቃቀምና መጠን በሰብልና በማዳበሪያ ዓይነት፣  በበልግ ወቅት በጊዜያዊ ሰብል የተያዘ መሬት ስፋት በሰብል ዓይነት፣ በበለግ ወቅት የተመረተ ምርት መጠን በሰብል ዓይነት እና የመሳሰሉት ሲሆኑ ከበጋ ወቅት መስኖ ናሙና ጥናት የሚሰበሰቡ መረጃዎችም በመስኖ እርሻ የተሸፈነ የመሬት ስፋት መጠን፣ በመስኖ ከለማው የመሬት ስፋት ላይ የተመረተው ጠቅላላ የምርት መጠን፣ በመስኖ ከሚለማው ማሳ ላይ የሚገኘው የምርታማነት መጠንን በሰብል አይነት በሀገር አቀፍ፣ በክልልና በዞን፤ የመስኖ እርሻ ሥራ አጠቃላይ ሁኔታ፣ በጥቅም ላይ የዋለ የማዳበሪያ ምርጥ ዘር፣ የአካባቢ ዘር፣ የፀረ-ሰብል መድኃኒትና መጠንን እንዲሁም የመስኖ ተጠቃሚ ቤተሰቦች ለመስኖ የሚጠቀሙት የውሃ ምንጭ ናቸው፡፡

ኤጀንው በ2013ዓ.ም የበልግና መስኖ ናሙና ጥናትን ለማካሄድ በታብሌት የተደገፈ የመረጃ አሰባሰብ ሂደትን ተግባራዊ ሲያደርግ በስልጠናም ሆነ መረጃ አሰባሰብ ላይ ኮቪድ-19 ቫይረስን ለመከላከል አስፈላጊውን ግብዓት በማዘጋጀት የመረጃ ሰብስቢወዎች ስልጠናን ለመስጠት እንዲሁም ጥናቱን ለማካሄድ ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡  

የበልግ ወቅት እርሻ ናሙና ጥናት የሚካሄደው ወካይ ከሆኑና በሳይንሳዊ መንገድ ከመላ ሀገሪቱ በተመረጡ 1,397 ቆጠራ ቦታዎች ከሚገኙ 27,940 ባለይዞታ ገበሬዎች ሲሆን የበጋ ወቅት እርሻ ናሙና ጥናትም ወካይ ከሆኑና በሳይንሳዊ መንገድ ከመላ ሀገሪቱ በተመረጡ 1,699 ቀበሌዎች ከሚገኙ በዘንድሮው በጋ ወቅት መስኖን ከተጠቀሙ ባለይዞታ ገበሬዎች ነው፡፡ ግብርና ለሀገሪቱ አጠቃላይ እድገት 42% በላይ አስተዋፅዎ የሚያበረክት የሀገሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት በመሆኑ ከጥናቱ የሚገኙትን መረጃዎች መንግስት በምርት ዘመኑ የሀገሪቱን ህዝብ መመገብ የሚችል ምርት መኖሩ/ አለመኖሩ ለማወቅ ፣ከዚህም በመነሳት እጥረት ካለ ረሀብ እንዳይፈጠር ቅድሚያ መፍትሄ ለማበጀት፣ ምርትና ምርታማነትን ወደተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገር ለሚያወጣቸው ዕቅዶችና ፖሊሲዎች እንደመነሻ ግብአትነት ይጠቀምበታል፡፡ ለተመራማሪዎችም የምርትና የለማ መሬት መጠኑን በማወቅ ለሚፈልጉት መረጃ መጠቀም እና ጥናቶችን ለማከናወንና በግብርና ዘርፍ ምርታማነት ዕድገት ላይ ለሚደረጉ ምርምሮች እንደመነሻ ግብአትነት ያገለግላል፡፡