መደበኛ ያልሆነ የስራ ዘርፍ ጥናትን ለማካሄድ ኤጀንሲው ዝግጅቱን አጠናቋል

ሶስተኛውን ዙር የሀገር አቀፍ መደበኛ ያልሆነ የስራ ዘርፍ ጥናት ለማካሄድ የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ከግንቦት 2-7/2013ዓ.ም በአዳማ፣ አምቦ፣ ሶዶ ፣ ደብረታቦር፣ ድሬዳዋና ሐዋሳ በሚገኙ የስልጠና ማዕከላት ለ700መረጃሰብሳቢዎች 232ተቆጣጣሪዎችና ለ23ስታቲስቲሽያኖች ለአንድ ሳምንት የሚቆይ ስልጠና ተሰጠ፡፡

ስልጠናውን በንግግር የከፈቱት የኤጀንሲው ቅ/ፅ/ቤቶች ዴስክ ሀላፊ አቶ አማን አብዱላሂብ እንደገለጹት መደበኛ ያልሆነ የስራ ዘርፍ በብዙ ሚሊዮን ለሚቆጠሩ ዜጎች የስራ ዕድል የተፈጠረበት ዘርፍ ሲሆን ለዘርፉ የተሟላ ፖሊሲ ለመቅረጽ የሚያስችል የስታቲስቲክስ መረጃ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው መረጃ ሰብሳቢዎች የሚሰጣቸውን ስልጠና በተገቢው መልኩ በመከታተል በመስክ ስራቸው ወቅትም ለመረጃው ጥራትና ወቅታዊነት አስፈላጊውን ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡

መደበኛ ያልሆነ የስራ ዘርፍ በተለያዩ የስራ መስኮች የሚካሄዱትን እጅግ በርካታ የምርት፣ የንግድና አገልግሎት ስራዎችን የሚያጠቃልል ሲሆን በዚህ ጥናት የስራ መስኩን ባለቤት ዲሞግራፊያዊ  ባህሪያት፣ መሰረታዊ መረጃዎች፣ የምርትና የሽያጭ ሁኔታ፣ የወጪ አይነትና መጠን፣ የሰራተኞች ብዛትና የቅጥር ሁኔታ፣ የመስኩ የወደፊት ዕቅድ፣ የትርፍ መጠኑና መሰል መረጃዎች ይሰበሰባሉ፡፡

ከጥናቱ የሚገኙ መረጃዎችም በዘርፉ የተሰማራውን ህዝብ ብዛትና ሌሎች ዝርዝር ሁኔታዎችን ለማወቅ የሚያስችል መረጃዎችን ለማግኘት፤ የስራ መስክ ዓይነቶችን ለመለየት፤ ብዛታቸውንና ስርጭታቸውን፤ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ያላቸውን ድርሻ፤ በስራው የሚተዳደሩትን ዜጎችና ያሉባቸውን ተግዳሮቶች ለማወቅና ዘርፉ በይበልጥ የስራ መስክና የገቢ ምንጭ እንዲሆን በመንግስት በኩል ለሚወጡ ፖሊሲዎችና መመሪያዎች እንደመነሻ ግብአትነት ያገለግላሉ፡፡

አገር አቀፋዊ መደበኛ ያልሆነ የስራ ዘርፍ ጥናት የሚካሄደው ወካይ ከሆኑና በሳይንሳዊ መንገድ ከመላ ሀገሪቱ በናሙና በተመረጡ 1,326 የቆጠራ ቦታዎች ከሚገኙ 39,780መደበኛ ባልሆነ የስራ ዘርፍ ከተሰማሩ ዜጎች ነው፡፡

ኤጀንው ጥናቱን ለማካሄድ በታብሌት የተደገፈ የመረጃ አሰባሰብ ሂደትን ተግባራዊ ሲያደርግ በስልጠናም ሆነ መረጃ አሰባሰብ ላይ ኮቪድ-19 ቫይረስን ለመከላከል አስፈላጊውን ግብዓት በማዘጋጀት ጥናቱን ለማካሄድ ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡

ለጥናቱ መረጃዎች በመስክ ከግንቦት09-30/2013 የሚሰበሰብ ሲሆን ሪፖርቱ ሀምሌ 30/2013 ዓ.ም ይፋ እንደሚደረግ ይጠበቃል፡፡