የኤጀንሲው ሰራተኞች ኤች አይ ቪ ኤድስ ፣ የነጭ ሪቫን እና የፀረ-ሙስና ቀንን በጥምረት አከበሩ

የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ አመራሮች እና ሰራተኞች የኤች አይ ቪ ኤድስ፣ የፀረ-ፆታዊ ጥቃት (የነጭ ሪቫን) እና የፀረ-ሙስና ቀንን ህዳር 30/2012 ዓ.ም በማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ የስብሰባ አዳራሽ ግንዛቤ በሚፈጥሩ ዝግጅቶች በጥምረት አክብረዋል፡፡

በዕለቱ የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወ/ት አበራሽ ታሪኩ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር የዘንድሮ የአለም የኤድስ ቀን “ማህበረሰቡ የለውጥ አቅም ነው፡፡” በሚል ሀገራዊ መሪ ቃል እንደሚከበር አስታውሰው የበዓሉ ዋና አላማም የኤች አይ ቪ ስርጭት እያደረሰ ስላለው ጉዳት የማህበረሰቡን ግንዛቤ ማስፋት እና ከኤድስ ነጻ የሆነ ትውልድን መፍጠር መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የነጭ ሪቫን ቀንም “ሴቶች እና ህጻናትን ከጥቃት በመጠበቅ ሁላችንም ሀላፊነታችንን እንወጣ፡፡” በሚል መሪ ቃል በሀገራችን ለ 14ተኛ ጊዜ በአለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ28ተኛ ጊዜ እንደሚከበርም የገለጹት ም/ዋ/ዳሯ የበአሉ ዋና አላማም ሴቶች የሚደርስባቸውን ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን በመከላከል እና በማስቆም ልማታዊ አስተዋጽኦ ማበርከት እንዲችሉ ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንደሆነ አያይዘው አብራርተዋል፡፡

በሀገራችን ለ15ተኛ ጊዜ በአለም አቀፍ ደረጃ ለ16ተኛ ጊዜ የተከበረውን የፀረ ሙስና ቀንንም “መልካም ስነምግባርን በመገንባት፣ ሙስናን በመታገል ዘላቂ ሰላም እና ልማትን እናረጋግጥ” በሚል መሪ ቃል የኤጀንሲው ሰራተኞች ያከበሩ ሲሆን ሙስና በሀገር አቀፍ ደረጃ ብሎም በኤጀንሲው ላይ የሚያስከትለውን አስከፊ ችግር የተቋሙ ሰራተኞች ከግንዛቤ በማስገባት ሊታገሉት እንደሚገባ ያሳሰቡት ም/ዋ/ዳሯ ዕለቱ በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት እና ተአማኒነት ያለው የስታቲስቲክስ መረጃን ከማቅረብ አንጻር እንደሚከበር አስታውቀዋል፡፡

ዛሬ በጥምረት የሚከበሩ ሦስቱ ጉዳዮች በሀገራችን በማህበራዊ፣በኢኮኖሚያዊ እና በመልከአ አስተዳደር ውስጥ እየፈጠሩ ያሉት ተግዳሮቶች ከፍተኛ እና ያልተሻገርናቸው በመሆኑ የሁሉንም ህብረተሰብ እና መንግስት ጠንካራ ቅንጅትና ተሳትፎ የሚፈልጉ ስለመሆናቸው ግንዛቤ በመያዝ እንደ ተቋም ስራችን ላይ እነዚህ ተግዳሮቶች የሚፈጥሩትን አሉታዊ ተፅዕኖ ለማስቆም በጋራ ተባብረን መስራት አለብን በማለት ገልጸዋል፡፡  

በመጨረሻም ወቅታዊ የኤች አይ ቪ ኤድስ መረጃ፣ የፀረ ሙስና አስከፊነት እንዲሁም የፀረ ጾታ ጥቃትን አስመልክቶ ፅሁፎች የቀረቡ ሲሆን የሻማ ማብራት ስነስርአት እና በቀረቡት ጽሁፎች ውይይት ተካሂዶ የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል፡፡